ጳጉሜ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት (ኦብነግ) እንደገለጸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ከአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች ከውጭ ለልማት በሚል ከሚለገሰው ገንዘብ በማንሳት 10 ሚሊዮን ብር መስጠቱ አስገራሚ ሆኖ እያለ፣ አሁን ደግሞ በደጋሃቡርና ቀብሪደሃር ወረዳዎች በመዘዋወር በአማራ፣ በኦሮምያና ጋምቤላ ለተሰማሩ ወታደሮች የእርድ ከብቶችን ህዝቡ እንዲያዋጣ እያስገደደ ነው ። ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ፕሮጀክት ከብት የማይለግስ ጎሳ ምህረት የለሽ ቅጣት እንደሚጣልበት አስጠንቅቀዋል። ከእርድ ከብት በተጨማሪ ወረዳዎች አዳዲስ ወጣቶችን መልምለው ለውትድርና ስልጠና እንዲልኩ ፕሬዚዳንቱ አዘዋል።
ኦብነግ በመላው ኦጋዴን ከ30 ሺ ያላነሱ ዜጎች መታሰራቸውን አስታውቋል። ድርጊቱ አገዛዙ ስልጣን ከእጁ እየወጣ መምጣቱን ያመላክታል ያለው ኦብነግ፣ የአንድ ክልል ወጣቶችን በመውሰድ በሌላው ክልል ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ በማድረግ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዲጋጩ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
ኦብነግ በኦጋዴንና በመላው ኢትዮጵያ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ በጽኑ አውግዞ ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲቆሙ እና ለነጻነታቸውና ለዲሞክራሲ እንዲታገሉ፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብም አገዛዙ ለፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቄ እንዲሆንና ጭፍጨፋው እንደቆም ጥረት እንዲያደርግ ኦብነግ ጥሪ አቅርቧል።