ኢሳት በሶስተኛ ሳተላይት ስርጭት ጀመረ

ኢሳት (ጳጉሜ 3 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ ሳተላይትና ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) አሁን ካሉት ሁለት የሳተላይት ስርጭት ፍሪኩዌንሲዎች (Satellite Frequencies) በተጨማሪ ሶስተኛ ፍሪኩዌንሲ በመከራየት የስርጭት አድማሱን ማስፋቱን ገለጸ።

“ኢሳት ባለፉት 6 እልህ አስጨራሽ አመታት የህወሃትን ቀቢጸ-ተስፋ የአፈና እንቅስቃሴ ተቋቁሞ የስርጭት አድማሱን በማስፋትና በማጠናከር ላይ ይገኛል” ያለው የኢሳት ማኔጅመንት መግለጫ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ኢሳትን ከአየር ላይ ለማውረድ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ዶላር መድቦ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም አልተሳካለትም ብሏል።

https://www.youtube.com/watch?v=_fqwrKdlsI0

ሆኖም፣ ሶስተኛ የሳተላይት ስርጭት መጀመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የህወሃት/ኢህአዴግ የአፈና ተግባር ለመቋቋም ጠንክሮ እየሰራ እንደሆነ ገልጿል። የኢሳት ደጋፊዎች እንዲሁም ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ኢሳት በከፍተኛ ወጪ የአፈና መረቦችን ሁሉ እየበጣጠሰ አገልግሎቱን መቀጠል እንዲችል ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲል ማኔጅመንቱ ጥሪውን አቅርቧል።

በኢሳት የሚተላለፉት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስርጭቶች የኢትዮጵያ ህዝብና አይን እና ጆሮ በመሆን ከፍተኛ አገልገሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ያለው የኢሳት ማኔጅመንት መግለጫ፣ አዲሱ ፍሪኩዌንሲ የኢሳት ቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

ሶስተኛ የኢሳት ፍሪኩዌንሲ Channel: SES 5, Downlink: 12034H, Symbol: 27500 Fec:  3 /4 መሆኑ ተገልጿል። በዚህና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የኢሳት ማኔጅመንት ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ ታውቋል።