የልጃቸውን ሁኔታ ለማወቅ ጥያቄ ያቀረቡ እናት በፖሊስ ድብደባ ተፈጸመባቸው

ኢሳት (ጳጉሜ 2 ፥ 2008)

አንድ ልጃቸው በቂሊንጦ እስር ቤት የታሰረባቸው እናት ረቡዕ የልጃቸውን ሁኔታ ለማወቅ ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ በፖሊስ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለሰዓታት ታስረው መቆየታቸው ለኢሳት ገልጸዋል።

“ልጄም ከሞተ አስከሬን ይሰጠኝ ብዬ በመጠየቄ በፖሊስ ድብደባ ተፈጽሞብኛል” ሲሉ የገለጹት እናት ለአምስተኛ ቀን የልጃቸውን ሁኔታ ባለማወቃቸው ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ሌላ አንዲት ሴት ልጅ በቃሊቲ እስር ቤት በእስር ላይ እንዳለች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ያስታውቁት እኚሁ እናት፣ ቅዳሜ በቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት አደጋው በደረሰ ጊዜ ለልጃቸው ምግብ ለማድረስ በስፍራው እንደነበሩና የተኩስ ድምፅ መስማታቸውን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የቤተሰብ አባልሎቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት በማቅናት ላይ የነበሩ ሌሎች የእስረኞች ቤተሰቦች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አክለው ገልጸዋል።

የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት በዚሁ የሃይል እርምጃ በርካታ የእስረኛ ቤተሰቦች ለእስር መዳረጋቸው ድብደባ የተፈጸመባቸው እንዲሁም እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በፈጸሙት ወከባ ምንም መረጃ ሳያገኙ ወደ ቤት መመለሳቸውን ያስረዱት የእስረኞች ቤተሰቦች ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ከሞራል እና ሰብዓዊነት አንጻር ምላሽ እንዲሰጣቸው በእንባ እየተናነቁ ጥያቄን አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ማክሰኞ የ18 አመት ልጃቸውን አስከሬን በህክምና ባለሙያዎች ተሸፋፍኖ የተሰጣቸው በመሆኑ ልጃቸው የሞተበትን ሁኔታ በአግባቡ መረዳት እንዳልቻሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

አብዛኛው የእስረኛ ቤተሰብ የእስረኛውን ሁኔታ እንዳላወቀ ያወሱት የሟች አባት በአደጋው ምክንያት ክፉኛ ሃዘን ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል።