በቂሊንጦ የእስረኞችን ሁኔታ ለመጠየቅ የሄዱ የእስረኛ ቤተሰቦች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እስርና ድብደባ ተፈጸመባቸው

ኢሳት (ጳጉሜ 2 ፥ 2008)

በቂሊንጦ እስር ቤት የሞቱትና የገቡበት ያልታወቀ እስረኞችን ሁኔታ ለማወቅ ረቡዕ ረፋድ ላይ ወደ ስፍራው በማቅናት ላይ የነበሩ የእስረኛ ቤተሰቦች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የመንግስት ባለስልጣናት ስለሞቱና ወደሌላ እስር ቤት ተላልፈዋል ስለተባሉ እስረኞች ረቡዕ መረጃን እንደሚሰጡ ቃል ቢገቡም በእለቱ መረጃው ለእስረኛ ቤተሰቦች አለመገልጹ ታውቋል።

ምላሽ ባለማግኘታቸው ስጋት ያደረባቸው የእስረኛ ቤተሰቦች ወደ ስፍራው ቢያመሩም የጸጥታ ሃይሎች የተሰባሰቡ ቤተሰቦችን ጉዞ ለማስተጓጎል ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ እናቶችንና የቤተሰብ አባላት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ለእስር ከተዳረጉት በተጨማሪም ሌሎች የታሳሪ ቤተሰቦች በፖሊስ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል።

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ከቀናት በፊት ቅዳሜ በእስር ቤቱ ስለደረሰው የእሳት አደጋና ስለተረፉ እስረኞች ሁኔታ ረቡዕ መረጃን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል።

ይሁንና ማረሚያ ቤቱ ስለተገደሉ እስረኞች ማንነትና ከአደጋው ስለተረፉ እስረኞች መረጃን ሳይሰጥ ቀርቷል።

ቅዳሜ ማለዳ በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ በእስር ቤቱ የተኩስ እርምጃ መካሄዱንና ከ20 የሚበልጡ እስረኞች መገደላቸው ተገልጿል።

ይሁንና መንግስት ስለተገደሉ እስረኞች ማንነት ረቡዕ ምሽት ድረስ የሰጠው መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የእስረኛ ቤተሰቦች መንግስት ችግራቸውን ተረድቶ የሟቾችን ማንነት ይፋ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በእስር ቤቱ የእሳት አደጋ በደረሰ ወቅት ያለ መሳሪያ በጥበቃ ላይ የነበረ የእስር  ቤቱ የጸጥታ ባልደርባ በዕለቱ የታጠቁ የጸጥታ አባላት በእስረኞች ላይ ያነጣጠረ የተኩስ ሩምታ መክፈታቸውን ማንነቱን በመደበቅ በሃገር ውስጥ ለሚታተም መጽሄት ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።