የብሪታኒያ መንግስት ዜጎቹ ወደ አማራና ጋምቤላ ክልሎች ሲጓዙ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ አሳሰበ

ኢሳት (ጳጉሜ 1 ፥ 2008)

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ እልባት አለማግኘቱን ተከትሎ የብሪታኒያ  መንግስት ዜጎቹ ወደ ክልሉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ ማክሰኞ በድጋሚ አሳሰበ። ከሶስት ቀን በፊት ለዜጎቹ ተመሳሳይ ማሳሰቢያን አሰራጭቶ የነበረው የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ አሁንም ድረስ ወደክልሉ በሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲያደርጉ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የሃገሪቱ ዜጎች በአማራ ክልል በሚያደርጉት የጉዞ ጥንቃቄ በተጨማሪ በጅጅጋ ከተማ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ስር በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወድ የብሪታኒያ መንግስት አሳስቧል።

በወረዳዎቹ ስላለው የጸጥታ ችግር ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠበው የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲማ፣ ጎጌ እና ኢታንግ ወረዳዎች ለደህንነት ስጋት መሆናቸውን አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ ሊዛመት ይችላል በሚል ለዜጎቿ ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ማሰረጨቱ ይታወሳል።

በሁለቱ ክልሎች ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ እልባት አለመግኘቱን ተከትሎ የተለያዩ የአለም አቀፍ ተቋማት ዜጎቻቸው ወደ ክልሎቹ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ እያሳሰቡ ይገኛል።