ጳጉሜ ፩ ( አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህዝባዊ እምቢተኝነቱን ጥሪ ተቀብለው በአስቸኳይ በተግባር ላይ ባዋሉት የተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች፣ የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። ምንም አይነት የመኪና እንቅስቃሴ የለም። ለወትሮው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው ከተሞች ዝምታ ሰፍኗል።
በርካታ ነዋሪዎችን በአጋዚ ጦር ያጡት የምስራቅ ሸዋ ከተሞች አርሶ፣ ኮፈሌና ዶዶላ የምስራቅ ሃረርጌዎቹ ሀሮማያ፣ አወዳይ ፣ ኮምቦልቻ፣ እንዲሁም አምቦ፣ ባሌሮቤ፣ ወለጋ ደንቢደሎ፣ ሳረቦቲ እና ሌሎችም ከተሞች ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ተግባራዊ እያደረጉ ነው።
የስራ ማቆም አድማው በአመት በአል ገበያ እና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽኖ የሚያመጣ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ በእነዚህ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴውን ለማስጀመር የጀመረው ጥረት አልተሳካለትም። በቄሌም ወለጋና በደንቢ ዶሎ ደግሞ ፖሊሶች የታክሲዎችንና የባጃጆችን ታርጋዎች ፈትተው ወስደዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን ተከትሎ የጤፍ እና ሌሎች የግብርና ውጤቶች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚሁ ዜና ሳንወጣ፣ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በርካታ ወጣቶች እየታሰሩ ነው። በባህርዳር፣ መራዊ፣ አዴት፣ ዱርቤቴ፣ ዳንግላ፣ ኮሰበር ፣ ቲሊሊ፣ ፍኖተሰላም፣ ደብረማርቆስ እንዲሁም በበርካታ የሰሜን ጎንደር ከተሞች በክልሉ የሰፈሩ ወታደሮች ወጣቶችን በሌሊት እያደኑ ወደ እስር ቤት እየወሰዱዋቸው ነው። በርካታ ወጣቶች በእስር ቤት ስቃይ እንየደረሰባቸው መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ቢፈልጉም አልቻሉም።
ወጣቶች ስቃይና እንግልቱ ቢበዛባቸውም ትግላቸውን ለመቀጠል በጠንካራ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ እየገለጹ ነው። በደብረታቦር ፖሊሶች ሳምንቱን ሙሉ ከጣቢያው እንዳይወጡ የተደረገ ሲሆን፣ ከተማውን የተቆጣጠሩት በአካባቢው ቋንቋ መግባባት የማይቸሉ ወታደሮች ናቸው። ወታደሮቹ መንገድ ላይ ባገኙዋቸው ወጣቶች ላይ ድብደባ እንደሚፈጸሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በሃረር ከተማ ደግሞ ኢብራሂም የተባለ ፖሊስ ከህዝቤ ጋር አብሬ እታገላለሁ፣ ህዝብ እየተገደለ መስራት አልፈልግም በማለት መለዮውን በመወርወሩ አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛል።