ጳጉሜ ፩ ( አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር የህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴው ለኢሳት እንደገለጸው በአሁኑ ሰአት የተለያዩ የስራ ማቆም አድማዎች እንዳሉ ተደርጎ የሚበቱ ወረቀቶች ወይም የሚተላለፉ የቃል መልእክቶች አስተባበሪ ኮሚቴው ያልጠራውና ሆን ተብሎ በገዢው ፓርቲ የሚደረግ የማምታቻ ጥሪ ነው። ህዝቡ ከአስተባባሪው ኮሚቴ ከሚሰጠው መግለጫ ውጭ በሌሎች መግለጫዎች እንዳይታለል የጠየቀው የአስተባባሪ ኮሚቴው፣ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርት ሲከፈት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት የኮሚቴውን ጥሪ እንዲሰሙ መልእክት አስተላልፈዋል።
ለህዝቡ መልካም አዲስ አመት የተመኘው አስተባባሪ ኮሚቴው፣ የህዝቡ ጥያቄ መሰረታዊ መልስ እስከሚያገኝ ድረስ ትግሉ በተለያዩ ስልቶች እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።
በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ለታዩት ህዝባዊ ንቅናቄዎች አድናቆትንና እና ምስጋናን የሰጠው ኮሚቴው፣ በኦሮምያ ለተጀመረው የስራ ማቆም አድማም ከፍ ያለ ምስጋናውን ገልጿል።
ለደህንነት ሲባል የኮሚቴውን ይዘት ይፋ ማድረግ ያልመረጠው አስተባባሪ ኮሚቴ፣ ከህዝቡ መሃል ያለ በመሆኑ ህዝቡ ድጋፍ እንደሚያደርግለት ገልጿል።