ኢሳት (ነሃሴ 30 ፥ 2008)
በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰን የእሳት አደጋ ተከትሎ ወደ ሶስት ሺ የሚጠጉ እስረኞች ለሶስተኛ ቀን የገቡበት አለመታወቁ አሳስቦት እንደሚገኝ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሰኞ አስታወቀ።
የእስረኞቹ ወደ ዝዋይና ሸዋ ሮቢት ተዛውረዋል ተብሎ ቢገለፅም፣ የታሳሪ ቤተሰቦት ወደ ስፍራው ሄደው እስረኞቹ እንደሌሉ ተነግሯቸው መመለሳቸውንና ድርጊቱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ተሾመ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
መንግስት እስረኞቹ ያሉበትን ሁኔታ እንዲሁም በእሳት ቃጠሎው ወቅት ሲካሄድ የነበረን የተኩስ እርምጃ ተከትሎ የሞቱ እሰረኞችን ቁጥር እስካሁን ድረስ ግልፅ አለማድረጉ ከህግ አንጻር ተገቢ አለመሆኑን ደግሞ የህግ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን አደጋ ምክንያት በማድረግ ከኢሳት ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቶ ተሾመ የታሳሪ ቤተሰቦች የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ እያደረጉ ያለው ጥረት ውጤት አለማገኘቱን ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው የቂሊንጦ እስር ቤት በርካታ ሰዎች የታሳሪ ቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ ቢጓዙም የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ህዝቡን ከሶስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ እንዳያልፉ ማድረጋቸው ታውቋል።
በርካታ አባላቱ በዚሁ እስር ቤት ይገኙበት የነበረው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ በእስር ቤቱ ወደ ሶስት ሺ የሚጠጉ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና ሌሎች እስረኞች ይገኙ እንደነበር ገልጿል።
ይሁንና የሁሉም እስረኞች ሁኔታ ለሶስተኛ ቀን ሰኞ ምሽት ድረስ ምንም ሊታወቅ አለመቻሉን ያስታወቀው ፓርቲው፣ በአባላቱና በእስረኞቹ ደህንነት እጅግ አሳስቦት እንደሚገኝ አክሎ አመልክቷል።
በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ የእስረኞች መብት አለመከበሩን የተናገሩት የፓርቲው አመራር አቶ ሙላቱ ተሾመ መንግስት ያለበትን ሃላፊነት እንዲወጣ በፓርቲውና በታሳሪ ቤተሰቦች ስም ጥሪን አቅርበዋል።
በቂሊንጦ እስር ቤት ቅዳሜ የተሰማን የተኩስ ድምፅ ተከትሎ በትንሹ 20 ሰዎች መገደላቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገኛኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን፣ የተለያዩ አካላት የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የህግ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው መንግስት በእስር ቤቱ የተፈጠረውን ድርጊት በአግባቡ ለህዝቡ አለማሳወቁ ከህግም ሆነ ከሰብዓዊነት አንጻር ተገቢ አለመሆኑን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዳሜ በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰን የእስት አደጋ ተከትሎ ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ እስረኞች መሞታቸውን BBC ሰኞ ዘግቧል።
በዚሁ እስር ቤት ደርሷል የተባለውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ በእስር ቤቱ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ መቆየቱን የዜና አውታሩ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን፣ በሃገሪቱ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆኑን አክሎ አመልክቷል።
የብሪታኒያው የማሰራጫ ጣቢያ ቢቢሲ የኢሳትን የቴለቪዥን ዘገባ ዋቢ በማድረግ በቂሊንጦ እስር ቤት የነበረን የእሳት አደታ ቃጠሎ በሪፖርቱ አስደግፎ አቅርቧል።
በዚሁ እስር ቤት በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ይገኙ እንደነበርና የደረሰ ጉዳት በአግባቡ ሊታወቅ አለመቻሉን የዜና አውታሩ አስነብቧል።