መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ከመጠን በላይ ያለፈ ሃይል መጠቀሙን  አሜሪካ ገለጸች

ኢሳት (ነሃሴ 30 ፥ 2008)

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር መንግስት ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ እየተጠቀመ መሆኑ እንዳሳሰባት አሜሪካ ገለጠች።

ይኸው ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የሃይል እርምጃ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ሃገሪቱ አበክራ መጠየቋን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ሳማንታ ፖወር ለአለም አቀፍ ጋዜጠኞች አስታውቀዋል።

በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አሜሪካና ምዕራባውያን ሃገራት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ውጥረት ዝምታን መርጠዋል በማለት ቅሬታን ሲያቀርቡ መሰንበታቸው ይታወቃል።

ይሁንና በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ህዝባዊ ተቃውሞ የሃገራቸው አቋም ይፋ ያደረጉት አምባሳደር ሳማንታ የአሜሪካ መንግስት ሰላማዊ ሰልፈኞች ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት ግልፅ ማድረጉን አክለው አስረድተዋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል በቆየውና በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው በዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞ ቁጥራቸው በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ አካላት በመግለፅ ላይ ሲሆኑ ሂውማን ራይትስ ዎች ከ500 በላይ ንጹሃን ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው በማሳወቅ ላይ ነው።

የአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ሲገልጽ ቢቆይም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲያሳውቅ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ ማቅናቱንና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ የአህጉሪቱ የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ እንደሚመክር አሶሼይትድ ፕሬስ ሰኞ ዘግቧል።

የአፍሪካ ህብረት ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳስቦት እንደሚገኝ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን፣ የህብረቱ አባል ሃገራትና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅታዊ መረጃን እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።