ነሃሴ ፴ ( ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ከስፍራው እንደዘገበው የእስርቤት ኃላፊዎቹ ትናንት ወደ ቂሊንጦ የሄዱ የታሳሪ ቤተሰቦችን “ ሁኔታውን እስከማክሰኞ ድረስ እናሳውቃችኋለን” ብለው የነበረ ቢኾንም፣ የልጆቻቸው፣ የአባቶቻቸው፣ የባለቤቶቻቸው፣ የእህቶቻቸው፣ የወንድሞቻቸውና የወዳጆቻቸው ሁኔታ አላስችል ብሏቸው ዛሬ ወደዚያው ሲያቀኑ “ እስከ አርብ ድረስ ጠብቁ” ተብለዋል።
ይህም ሳይበቃ ታጣቂዎቹ የእስረኞችን ቤተሰቦች በመስደብ፣ በመገፍተር፣ በማዋከብና ዱላ በመጠቀም እንዲበተኑ አድርገዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው የአቶ ዮናታን ተስፋዬ እናት “ ልጄ እንዴት ሆኖ ይሆን?’ ብለው አንዱን ኮማንደር ሲጠይቁት ተገቢ ያልሆነ ምላሽ ከመስጠቱም በላይ አንገታቸውን በስካርቫቸው በማነቅ “ ውሰዱና አስገቡልኝ!” ማለቱን ተከትሎ እጅግ ያዘኑት የዮናታን እናት ፦” ለመሆኑ ሀገሬ ዬት ነው?” ብለው በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ኮማንደሩ ከዚህም ባሻገር የዮናታን እናት ለጆሮ እጅግ ጸያፍ የሆኑ ስድቦችን የሰደባቸው ሲሆን፤ በስፍራው የነበሩ የታሳሪ ቤተሶችና ወዳጆች በሁኔታው እጅግ ማዘናቸው ታውቋል።
ቅዳሜ በቂሊንጦ እስር ቤት እሳት መቀስቀሱን ተከትሎ እስረኞች እንደተገደሉ መዘገቡ ይታወሳል። በወቅቱ አንዳንድ የሀገር ውስጥ ፕሬሶች የሟቾቹ ቁጥር 20 እንደሆኑ የዘገቡ ቢሆንም፣ ዘግይተው ከተለያዩ ሆስፒታሎች የሚወጡ መረጃዎች ግን የሟቾች አሀዝ ማሻቀቡን ያመለክታሉ።
የዓይን ምስክሮች እንዳሉት በቂሊንጦ እሳት ከመነሳቱ ከአንድ ቀን በፊት የእስር ቤቱ መደበኛ ጠባቂዎች እንዲነሱና በምትካቸው ሌሎች እንዲመጡ የተደረገ ሲሆን፤ ግድያውን የፈጸሙትም እነዚሁ ተተኪዎቹ አዲስ ታጣቂዎች ናቸው።
ስለጉዳዩ እንኳን የታሳሪ ቤተሰቦች ህዝብም ወዲያውኑ የማወቅ መብት ቢኖረውም መንግስት እስካሁን ድረስ እውነታውን ለማሳወቅ አልደረም።
ይህም በታሳሪ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ጭንቀትና ሀዘን እንደጨመረባቸው ይናገራሉ።
የህሊና እስረኛው የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት ወይዘሮ ሀና ቀኑንም፣ ሌሊቱንም በጭንቀት እንደሚገኙ ይገልጻሉ፦
ቂሊንጦ-የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን፣ የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ታሳሪዎች የሚገኙበት እስር ቤት ነው።