በደሴና በኮምቦልቻ ወጣቶች እየታሰሩ ናቸው

ነሃሴ  ( ) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ  ከቀትር በኋላ በደሴ ከተማ የተጀመረውን የሥራ ማቆም አድማ ለማደናቀፍ የጸጥታ ኃይሎች በግዳጅ አንዳንድ የንግድ ተቋማትን ማስከፈት ጀምረዋል።

ከዚህም ባሻገር  ሕዝባዊ እቢተኝነቱን ያስተባብራሉ የተባሉ ወጣቶች በተናጠል እየታሰሩ መሆናቸው ታውቋል።

የከተማዋ ነጋዴዎች የማዋከብና የማስፈራራት ሰለባ ቢሆኑም  የደሴ ከተማ  የፀጥታ ድባብ ውስጥ መወደቋን ምንጮቻችን አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮምቦልቻ የተቃውሞ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ሹመኞች ሰሞኑን ነጋዴዎችን እና የመንግስት ሰራተኞችን ሰብስበው አስፈራርተዋል።

አርብ ዕለትም  በከንቲባው ጽ/ቤት የዞንና የወረዳ ባለሥልጣናትና  ከነጋዴዎች ጋር የተሰበሰቡ ሲሆን፤ ከንቲባው ደነቀ ምትኩና ም/ከንቲባው አቶ አዲሱ ነጋዴዎችን በግልጽ አስፈራርተዋል።

ስብሰባው “ድርጅቶቻችሁን ብትዘጉ ንግድ ፈቃዳችሁን እንቀማለን፣ እርምጃ እንወስዳለን” በሚለው የከንቲባዎቹ ዛቻ ቢጠናቀቅም፤ ህብረተሱቡ በተለይም ወጣቱ የለውጥ ጥያቄውን ሊያቆም ባለመቻሉ ትናንት እሁድ ምሽት  የከተማዋ ወጣቶች በታጣቂዎች እየታፈሱ ተወስደዋል።

በከተማዋ አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢም እሳት መነሳቱን ተከትሎ ትናንት ምሽቱን ከተማዋ ሙሉ በሙሉ መብራት ጠፍቶባት በጨለማ ተውጣ አምሽታለች።

ደብረብርሃንና በአጣዬም ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በቅርቡ እንደሚጀመር በመነገር ላይ ነው።