ነሃሴ ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአጋዚ ወታደሮችም በህዝብ ላይ እየተኮሱ ነው።
የሰሜን ጎንደር ከተሞች ደባርቅና አምባጊዮርጊስ ዛሬ ከወትሮው በተለየ ከአጋዚ ወታደሮች፣ ከታጣቁ የአካባቢ ሚሊሺዎች ጋር ሲፋለሙ ውለዋል።
በደባርቅ ከትናንት ጀምሮ ሲካሄድ በዋለው ህዝባዊ አመፅ 4 ሰዎች ሲገደሉ ከ17 በላይ ቆስለዋል። ባለፈው ሰኞ ነሃሴ 23፣ 2008 ዓም አንድ ዘይት እና እህል የጫነ ተሽከርካሪ በከተማው ነዋሪዎች እንዲቆም ተደርጎ ዘይቱና እህሉ እንዲከፋፈል ተደርጎ መኪናውን የተቃጠለ ሲሆን፣ ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ በቀጥታ ተኩሰዋል። ትናንት ህዝቡ የተገደሉትን ቀብሮ ሲመለስ የከንቲባውን፣ የወረዳውን የጸጥታ ሃላፊውንና በድብደባ የተሳተፉ 2 ታጣቂዎች ቤቶች ተቃጥለዋል። በዚህ የተበሳጩት ወደ አካባቢው የገቡት ወታደሮች የአገር ሽማገሌዎች፣ ህጻናት ፣ ሴቶች ሳይቀሩ እየደበደቡ ነው
በአምባጊዮርጊስ ከተማ ከትናንት ከሰዓት እስከ ዛሬ ጠዋት 1፡30 ጋር ገበሬው ከታጣቂ ሚሊሺያውና ከፖሊስ ጋር ሲታኮስ አድሯል። አንድ ልጇቿን ለማፈላለግ የወጣች እናት በጥይት ተመትታ ህይወቷል ሲያልፍ 8 ፖሊሶችና 12 አርሶአደሮች ቆስለዋል።
በተመሳሳይ ቀይ ኮፍያ ያደረጉ ወታደሮች ከአካባቢ ሚሊሺያዎች ጋር በማበር በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ሲፈጽሙ መዋላቸውን አካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በጋይንት ደግሞ የገጠሩ እና የከተማው ህዝብ በጋራ በመሆን ከወሎ የተነሳውን የአጋዚ ወታደር ወደ ጎንደር እና ጎጃም እንዳይሻገር ለማድረግ አንድ አነስተኛ ድልድይ በመስበር ወታደሮች እንዳይጓዙ አድርገዋል። አርሶአደሩ ከከተማው ህዝብ ጋር በመጣመር ከፍተኛ ጥበቃ በማድረግ ላይ ነው።
በባህርዳር ህዝቡ ቤቱ በመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ተቃውሞውን እየገለጸ ሲሆን፣ ትናንት ከፍተኛ የተኩስ ለውውጥ ሲደረግበት በነበረው ቀበሌ 14 አካባቢ ዛሬ ከሰአት ጀምሮ ተኩሱ መቆሙን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በርካታ የውጭ አገር ባለሀብቶች እና የብአዴን ንብረት የሆኑ የአበባ እርሻዎች የሚገኙ ሲሆን፣ መሬታቸውን በግዳጅ የተነጠቁ አርሶአደሮች የተለያዩ ኩባንያዎችን መኪኖች በእሳት አቃጥለዋል። ሁለቱ የህንድ ባለሃብቶች የአበባ እርሻቸው ተቃጥሎአል። በአርሶአደሮችና በወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ አርፍዷል።
በመርአዊ ጊዜያዊ የጎበዝ አለቆችን ለመምረጥ ስብሰባ ተጠርቶ የነበረ ቢሆንም፣ በአካባቢው ካሉ ፖሊሶች ጋር አለመግባባት በመከሰቱ ስብሰባው ለሌላ ቀን ተላልፏል።
በደብረማርቆስ የቤት ውስጥ የስራ ማቆም አድማው ተጠናክሮ በመቀጠሉ በአሁኑ ሰአት ምንምም አይነት እንቅስቃሴ አይታይም።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት ወደ አማራ ክልል መግባቱንና እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን ተከትሎ፣ ህዝቡ ተቃውሞውን ወደ ቤት ውስጥ አድማ በመቀየር በአብዛኛው የክልሉ ከተሞች ምንም እንቅስቃሴ አይታይም።
በበርካታ ከተሞች የጎበዝ አለቆች አሁንም ከተሞችን እያስተዳደሩ ሲሆን፣ ለህዝብ የሚጥቅሙ ውሳኔዎችን እያሳለፉ እንቅስቃሴውን በመምራት ላይ ናቸው።
በደቡብ ጎንደር የአካባቢ ሚሊሺያ የብአዴን ታጣቂዎች የውሎ አበል ተከፍሎአቸው በወጣቶች ላይ ጉዳት እያደረሱ ሲሆን፣ ህዝቡም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በደብረታቦር ሳጅን አለምነው ገላየ የተባለ ፖሊስ ከህዝብ ወገን ቆመሃል በሚል በዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አለባቸው ትእዛዝ ተይዞ ታስሯል። በባህርዳርም የብአዴን አባላት አንዳንድ ግለሰቦች ወጣቶችን እየጠቆሙ ማሳሰር በመጀመራቸው የከተማው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ እየሰጡዋቸው ነው።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ያሉ ከ21 ሺ ያላነሱ የክረምት ተማሪዎች ዛሬ ግቢያቸውን ለቀው በመውጣት ወደ መጡበት አካባቢ ተመልሰዋል።