ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)
በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ግንባር ቀደምትነት በኢትዮጵያ በስራ ላይ እየተተገበረ ያለው ያለው ፌዴራሊዝም፣ አዋጪነቱ በምዕራብያውያን ዲፕሎማቶችና የፖለቲካ ተንታኞችን አጠያያቂ እየሆነ መምጣቱ ተነገረ።
ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለው ፌዴራሊም በኢትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ እንዲውል ያደረገው፣ አገራዊ አጀንዳ ያላቸው ድርጅቶች እንዳያንሰራሩ ለመደፍጠጥ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በቀጣይ ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ብሄር ተኮር ተቃውሞዎችን ከፋፍሎ ለመምታት ታስቦ እንደሆነ ፎሪይን አፌይስ ትናንት ባወጣው ዘገባ አስረድቷል። ድርጊቱ ለተወሰኑ አመታት ተግባራዊ ሆኖ አዋጪ መስሎ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያን ወደ ውድቀት ጎዳና እየመራት እንደሆነ በድረገጹ ላይ የወጣው ትንታኔ ያስረዳል።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ አለምና መንግስት-መር እድገትን የሚከተል ህወሃት/ኢህአዴግ፣ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ይገኛል ያለው የForeign Affairs ዘገባ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተከሰተ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ የድርጅቱ ህጋዊነትና እያስከተለ ያለው ፌዴራሊዝም አፈጻጸም ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን በዝርዝር አስፍሯል። ህወሃት/ኢህአዲግ የአማራ መንግስታትን በመቃወም የተመሰረተ ድርጅት መሆኑን የገለጸው ፎሪን አፌይርስ፣ በቁጥር አነስተኛ ከሆነው የትግራይ ክልል የመጣው ህወሃት በፌዴራል መንግስት የበላይ ሆኖ እየመራ እንደሚገጽ በጹሁፍ አስፍሯል።
ከዚህ በፊት በኦሮሞያና በሌሎች ክልሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደረገ የቆየ ቢሆንም፣ በአማራ ክልል የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ በህወሃት አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያመጣ እንደሆነ ይኸው ድረገጽ ዘግቧል።
በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉት በኢኮኖሚ መሻሻል ያሳዩ የባህርዳርና የአዳማ ከተሞች ጭምር መሆኑን የገለጸው የፎሪን አፌይርስ ዘገባ፣ ህወሃት/ኢህአዴግ እየተከተለ ያለው የብሄር ፌዲራሊዝም አዋጪነት ከፍተኛ ፈተና ተጋርጦበታል ብሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች በመፈጠራቸው የወደፊቷ ኢትዮጵያ ህገመንግስት ላይ እንኳን ገና መስማማት እንደሚያስፈልግ የገለጸው ፎሪን አፌይርስ፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል ለመተንበይ አስቸጋሪ ፈተና ተጋርጦበታል በማለት ዘግቧል።
ኢህአዲግ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ፈተና እንደተጋረጠበት የሚናገረው ይህ ጹሁፍ፣ ኢትዮጵያን ለ21 አመታት በአምባገነንት የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ የአመራር ክፍተት በመተዋቸው በአገዛዙ ባለስልጣናት አለመደማመጥ መኖሩም በምሳሌ አስረድቷል። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በዘንድሮው አመት በኦሮሚያ ለሞቱት ሰዎች አዝኛለሁ፣ የግድያ ድርጊትም ከዚህ በኋላ ይቆማል ቢሉም በህወሃት ቁጥጥር ስር ያለው ጸጥታ ሃይል በኦሮሞዎች ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የግድያ ድርጊቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የማዘዝ ስልጣን እንደሌላቸው ትዝብቱን ያስቀመጠው ፎሬን አፌይርስ፣ የህወሃት ተቀጽላ የሆኑት የክልል ፓርቲዎች መሪዎች በሙስና የተጨማለቁ በመሆናቸው ምክንያት በህዝቡ የተናቁ በመሆናቸው ተቀባይነት አጥተዋል በማለት ይገልጻል።
የተከፋፈለ የፖለቲካ ማዕከላዊነት፣ አወዛጋቢ የክልል ልሂቃን መብዛት፣ የነጻ አውጪ ትግልና የማርሲዝም ሌኒኒዝም ቅሪት ተደማምሮ አሁን በአገሪቷ ለተከሰተው ከፍተኛ ሁከት መንስዔ መሆኑን ጽሁፉ በዝርዝር አስረድቷል።
በህዝባዊ እምቢተኝነቱ የተሳተፉም ያልተሳተፉም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሁን በስራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሜዳ እኩል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ማገዱን ጽሁፉ አጠቃሏል።