ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)
የጅቡቲ መንግስት በአገሩ የሚገኙ በመቶዎችን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለኢትዮጵያ አሳልፎ እንዳይሰጥ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተማጽኖ አቀረበ። ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ በግዳጅ የሚመለሱ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሰቆቃ፣ እስራት ወይም ግድያ ሊደርስባቸው ይችላል ሲል ገልጿል።
የጅቡቲ መንግስት ብዛት ያላቸው የአማራና የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስሮ እንደሚገኝ የገለጸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ፣ ስደተኞችን ወደኢትዮጵያ በግዳጅና በጅምላ የመመለስ ሂደት በየቀኑ ሲከናወን የነበረ ድርጊት መሆኑን ገልጿል።
በጅቡቲ የሚደረገው የጥገኝነት ጥያቄ የምዝገባ ሂደት በጣም አዝጋሚ ነው ያለው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ፣ ከዚህ በፊት የተመዘገቡት ስደተኞች ጭምር የስደተኝነት ዕውቅና ሳይኖራቸው እየተንከራተቱ እንደሚገኙ አትቷል። በመሆኑም በጅቡቲ የሚኖሩ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ለመሆናቸው ምንም አይነት መረጃ እንዳልተሰጣቸው የአምነስቲ ሪፖርት አስነብቧል።
በተለይም በኦሮሚያ በአማራ ክልሎች ከሃምሌ 30 እና ነሃሴ 1 ፥ 2008 ዓም ከተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች በኋላ ብዛት ያላቸው በጅቡቲ ጥገኝነት የጠየቁ ሰደተኛ ኢትዮጵያውያን በግዳጅ ወደኢትዮጵያ እንዲመለሱ እየተደረገ እንደሆነ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ያስረዳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ የሚኖሩ ኢትይጵያውያን በአገር ውስጥ የሚደረጉትን ሰልፎች ያስተባብራሉ በማለት ክስ እንደሚያቀርብ የገለጸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ከዚህ በፊት በግዳጅ ከጅቡቲ የተመለሱ የአማራና የኦሮሞ ስደተኞች በመንግስት ሃይሎች ምን እንደደረሰባቸው አለማወቁን ድርጅቱ በድረገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ አስታውቋል።
የጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ሰቆቃ፣ ግድያ ወይም እስራት ሊደርስባቸው እንደሚችል የገለጸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ስደተኞ ኢትዮጵያውያኑ በግዳጅ ወደኢትዮጵያ መመለስ የአለም አቀፍ ህግን ስለሚጻረር የጅቡቲን መንግስት ድርጊት ተቃውሟል።
በመሆኑም የጅቡቲ መንግስት የታሰሩትን እንዲለቅና ወደ ኢትዮጵያ ሊመልስ ያሰባቸውን ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ መብት እንዲያከብር ተማጽንዖ አቅርቧል።