ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 816 ስደተኞች በሱዳን ቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢሳት (ነሃሴ 25 ፥ 2008)

በሱዳንና ሊቢያ ድንበር ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት በህገወጥ መንገድ ሲጓዙ ነበሩ የተባሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ80 በላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ስደተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሱዳን የጸጥታ ሃይል ባለስልጣናት አስታወቁ።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከሰኔ 27 እስከ ነሃሴ 16 2016 ድረስ 816 የአፍሪካ ስደተኞች በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ መታሰራቸውን የሱዳን ፖሊስ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዥ ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸው ታውቋል።

ከስደተኞቹ መካከል 347 ኤርትራውያን፣ 130 ኢትዮጵያውያን እና 90 ሱዳናውያን የሚገኙበት ሲሆን፣ 10 ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ከተጋጩ በኋላ በቁጥር ስር መዋላቸው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) የተባለ የዜና አውታር ትናንት ማክሰኞች ዘግቧል።

በህወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እና በሱዳን መንግስት ወታደሮች መካከል በተደረገው ውጊያ ሶስት የሱዳን መንግስት ወታደሮች መሞታቸው ሲታወቅ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት ስደተኞች ወደ አገራቸው በግዳጅ ከመመለሳቸው በፊት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ጄኔራል አዋድ ዳህያ የተባሉ የሱዳን ፖሊስ ኮሚሽነር ተናግረዋል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ኮሚንሽንን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ ስደተኞቹን ለመቆጣጠር በድንበሮች የሚያካሄደው ቁጥጥር ችግሩን ካለመቅረፉም በላይ ስደተኞችን ለአምባገነን መንግስታት መመለስ ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ መጣል ይሆናል በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።

ከወራት በፊት በኦሮሚያ በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች በስደት ወደ አውሮፓ እና ወደ አረብ አገራት መጉረፋቸው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሃላፊዎች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዘጠኝ የመካከለኛና የምስራቅና አፍሪካ አገራት ጋር ትብብር በመፍጠር የስደተኞችን ፍሰት ለመቀነስ 70 ቢሊዮን የእርዳታ እቅድ እንደሚሰሩ ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸውን ከዚህ በፊት ዘግበን ነበር።