በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደሌሎች ቦታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት አድማሱን አስፍቶ በሰላማዊ ሰልፍና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ዛሬ ማክሰኞች ብዛት ባላቸው የአማራ ክልል ከተሞች እየተካሄደ እንደሆነ ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በምዕራብ አማጭሆ አብርሃ ጅራ የተጀመረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ አብደራፊና አጎራባች አካባቢዎች ተዛምቶ ህዝቡ ከአገዛዙ ወታደሮች ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

በጋይንት፣ ደብረታቦር፣ ወረታና ሃሙሲት የስራ ማቆም አድማ እና የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ እየተደረገ እንደሆነ ለኢሳት የደረሰው መረጃ የመላከተ ሲሆን፣ በእብናት ወረዳ ህዝቡ በነቂስ በመውጣት የታሰሩትን ሰላማዊ ዜጎች ማስለቀቁ ታውቋል።

በባህርዳር ሰሞኑን ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞ ዛሬ ማክሰኞችም የቀጠለ ሲሆን፣ የከተማው ህዝብ በዛሬው ዕለትም ተቃውሞውን በአደባባይ ሲገልጽ እንደዋለ ለማወቅ ተችሏል። በዚሁ የባህር ዳር ሰልፍ ላይ የአጋዚ ጦርና መደበኛ ሰራዊት በህዝቡ ላይ በቀጥታ በመተኮስ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

በመራዊ ከተማ ትናንት የተጀመረው ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬ ማክሰኞ ቀጥሎ እንደሚገኝ የገለጹት የኢሳት ምንጮች፣ የመንግስት መከላከያ ሰራዊት በተኮሰው ጥይት ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

በአዊ ዞን በጃዊ ወረዳና አንከሻ ወረዳ አዮ ከተማ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተደረገ ሲሆን ወታደሮች በህዝቡ ላይ ሲተኩሱ እንደዋሉ ከስፍራው የደረሰን መረጃ የመለክታል።

በምዕራብ ጎጃም የምትገኘው ፍኖተ ሰላም ከተማ በከፍተኛ ውጥረት እንደምትገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

በይልማ ዴንሳ አዴት ከተማ፣ በመሸንቲ ህዝቡ የራሱን አመራሮች የመረጠ ሲሆን፣ በሌሎች አካባቢዎችም የጎበዝ አለቃ እየተመረጠ እንዲያስተዳድር እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ማክሰኞ በጎንደር አምባ ጊዮርጊስ 550 ሳጥን ቢራ በሰላማዊ ሰልፈኞች መውደሙን ተከትሎ የመንግስት መደበኛ ወታደሮች ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ መዋላቸው የአይን ዕማኞች ከስፍራው ዘግበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት እየተደረገ ባለው የነጻነት ትግል፣ በባህርዳር፣ በዳንግላ፣ በእንጅባራ (ኮሶበር)፣ በቲሊሊ፥ በአዴት፣ በቻግኒ፣ መራዊ፣ መሸንቲና በመሳሰሉ ከተሞች ከፍተኛ ህዝባዊ እምቢተኝነት እየተካሄደ ሲሆን፣ ህዝባዊ ተቃውሞው በሌሎችም አካባቢዎች አድማሱን አስፍቶ መቀጠሉ ታውቋል።

በአማራ ክልል በህዝባዊ እምቢተኝነት የተሳተፉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ለአጋዚ ገዳይ ቡድን መረጃ ሲያቀብሉ በነበሩትና ከህወሃት/ብዓዴን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው መዘገባችን የሚታወስ ነው።