በአማራ ክልል የሚካሄዱ ህዝባዊ አመጾች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ነሃሴ  ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር የተጀመረውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ወታደሮች ለችግረኛ ወጣቶች እርዳታ ለማሰባሰብ በሞከሩ ወጣቶች ላይ በወሰዱት እርምጃ ህዝቡ በመቆጣት ከተቃውሞውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ውሎአል።

ከባህርዳር በ15 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ መሸንቲ ከተማ ደግሞ 2 አበባ እርሻዎችና የተለያዩ መኪኖች ተቃጥለዋል። አካባቢው ለትራንስፖርት ዝግ ሆኗል።

ከባህርዳር በ30 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ መራዊ ከተማ፣ የከተማው ነዋሪ ከአርሶአደሮች ጋር ተቀናጅቶ በመውጣት ከተማዋን ተቆጣጥሮ ውሎአል። የተለያዩ ባለስልጣናት ቤቶች ተደብድበዋል ተቃጥለዋል።

ከባህርዳር በ80 ኪ ሜ ርቀት በምትገኘዋ ዳንግላ ከተማም ከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ እና ወኪል ናቸው የተባሉ ሰዎች ቤቶቻቸው ተቃጥሎአል።

በአዊ ዞን፣ በእንጅባራ፣ ቻግኒ በአንከሻ ጔጉሳ  ወረዳ በሁዲት እና በአዮ ፣ በቲሊሊ እና ሌሎችም አጎራባች ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞ ተካሂዷል። በቋሪት ህዝቡ የጎበዝ አለቃውን መርጦ በራሱ እየተዳደረ ነው።

በአዴት ከተማም እንዲሁ ህዝቡ አስተዳደሪዎችን አባሮ በራሱ እየተዳደረ ነው። በማክሰኝት የበለሳ አርሶአደሮች ከፌደራል ፖሊሶች ጋር ተታኩሰዋል። ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ነው።

በጋይንት ወጣቶች በራሳቸው መተዳደር ጀምረዋል። አካባቢውን በሙሉ ከትራንስፖርት ውጭ አድርገዋል።

ደብረታቦር፣ ሃሙሲትና ወረታም የቤት ውስጥ አድማውን ጀምረዋል። ወታደሮች በጉማራ ላይ የደረሰባቸውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመበቀል ሃይል ለማንቀሳቀስ ቢሞክሩም መንገዶች በመዘጋጋታቸው አልቻሉም።

በወገራ ወረዳ አምባ ጊዮርጊስ ከተማ ደግሞ ዳሸን ቢራን የጫነ አንድ ኤፍ አሴር መኪና በከተማው ህዝብ እንዲቆም ተደርጎ ቢራው ሙሉ በሙሉ ወርዶ እንዲደፋ ከተደረገ በሁዋላ፣ ሹፌሩ  ተለቋል።

ገደብየ ህዝቡ በራሱ ለመመራት ውሳኔ አስተላልፏል ። 10 የኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል።

ተቃውሞውን አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ በርካታ ወታደሮች በህዝብ ላይ አንተኩስም በማለታቸው የቀን አበል የሚከፈላቸውን  ሚሊሺያዎች የወታደር ልብስ እያለበሱ ቦታቸውን እየያዙ ነው።

ባለፉት 3 ቀናት ብቻ 30 ያክል ወታደሮች ጠመንጃዎቻቸውን አስረክበው መጥፋታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።