ኢሳት (ነሃሴ 23 ፥ 2008)
ባለፉት ሳምንታት በአማራ ክልል በሚገኙ በተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሳምንቱ መገባደጃ በአዊ፣ በምዕራብ ጎጃምና፣ በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ትናንት እሁድና ዛሬ ሰኞች ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።
ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት እየተደረገ ባለው የነጻነት ትግል፣ በባህርዳር፣ በዳንግላ፣ በእንጅባራ (ኮሶበር)፣ በቲሊሊ፥ በአዴት፣ በቻግኒ፣ መራዊ፣ መሸንቲና በመሳሰሉ ከተሞች ትናንት እሁድና ዛሬ ሰኞ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል።
እሁድ በህዝባዊ ተቃውሞ የተሳተፉ ሰላማዊ ሰልፈኞች “በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚደረግ ግድያ እናወግዛለን፣ ወያኔ አይገዛንም፣ ደመቀ መኮንን አይወክለንም” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ መዋላቸውን እሳት ያነጋገራቸው እማኞች ከስፍራው ገልጸዋል።
በእንጅባራ (ኮሶበር) ከተማ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አደባባይ የወጣውን የከተማዋን ነዋሪ ለመበተን የተኩስ ዕርምጃን ጨምሮ የተለያዩ የሃይል እርምጃዎችን በመጠቀማቸው ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው የታወቀ ሲሆን፣ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ከባድና ቀላን የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የኢሳት ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል።
በቲሊሊ ከተማ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ህዝቡ በነቂስ በመውጣት እስረኞችን ማስፈታቱ የተነገረ ሲሆን፣ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ አካባቢው በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በአማራ ክልል በህዝባዊ እምቢተኝነት የተሳተፉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ለአጋዚ ገዳይ ቡድን መረጃ ሲያቀብሉ በነበሩትና ከህወሃት/ብዓዴን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው ለማወቅ ተችሏል። በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የተማረሩ ወጣቶች በአካባቢያቸው ወጣቶችን በመጠቆምና በማስያዝ በስለላ የተሰማሩ ሰዎችን መኪና አቃጥለዋል፣ ንብረታቸውንም አውድመዋል።
በዳንግላ ከተማ እሁድ ዕለት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ፣ አንዲት የህወሃት አባል በወሰደችው የሃይል ዕርምጃ፣ በርካታ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ማቁሰሏ ታውቋል። በድርጊቱ የተበሳጩት የአካባቢው ነዋሪዎች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በእንጅባራ ከተማ ለህወሃት ሲሰልሉ የነበሩ የህወሃት ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ንብረትም ሰላማዊ ሰልፈኞች በወሰዱት እርምጃ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ታውቋል።
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ዕሁድ በራስ ተነሳሽነት ለሰላማዊ ሰልፍ በነቂስ የወጣው ሰላማዊ ሰልፈኛ፣ ባለ ኮከቡን ባንዲራ በማውረድ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባለው ባንዲራ ተክቷል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ህወሃትንና የብዓዴንን ከፍተኛ አመራር አባላት ሲያወግዙ እንደነበር ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።