ነሃሴ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምዕራብ ጎጃም ዞን በፍኖተሰላም ፣ ጅጋና ማንኩሳ ከተሞች ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሄድ ከቆዩ በሁዋላ፣ ተቃውሞው ወደ አጎራባች ከተሞች በመሸጋገር ዛሬ አርብ በቡሬና ቋሪት ከተሞች ተቀጣጥሎ ህዝቡ ከወታደሮች ጋር ሲፋለም ውሎአል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በቡሬ ሲሆን አንድ ሰው ሲገደል ከሶስት አላነሱ ቆስለዋል። አንዳንድ ወገኖች የሞቱት ሰዎች ቁጥር 2 ነው ይላሉ።
የብአዴን የንግድ ድርጅቶች የሆኑት አባይ ባንክና የአማራ ብድር ቁጠባ ተቋም እንዲሁም የብአዴን ምልክቶች በድንጋይ ተደብድበዋል። በቋሪት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶ ግራፍ ተቃጥሎአል። በከተማው የተሰቀለውን ሰንድ አላማ በማውረድም ምንም ምልክት በሌለው ሰንደቅ አላማ ተክተዋል። የፖሊስ ሃይሎች ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው ታውቋል።
ፍኖተሰላም ከተማ ሃሙስ ተደርጎ በነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ የተገደለው የመምህራን ኮሌጅ ተማሪ አወቀ ሞሴ አስከሬን ቤተሰቦቹ ወደ ሚኖሩበት ሞጣ ከተማ ተልኳል። የከተማው ነዋሪዎች ገዳዩ ፖሊስ ተላልፎ ይሰጠን በማለት ቢጠይቁም፣ ከብር ሸለቆ ወታደራዊ ካምፕ የመጡት ወታደሮች ግን ፖሊሱን ከህዝብ እይታ ሰውረውታል።
በሰሜን ጎንደር ዞን በጎንደር ፣ ዳባት እና ደባርቅ የተጠራው የስራ ማቆም አድማ አሁንም ቀጥሎአል። ህዝቡ አድማውን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ የኢህአዴግ እና የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ህዝቡ አድማውን እንዲያቆም ተማጽነዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትናንት ምሽት ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ ታስረው በሚገኙበት የጎንደር እስር ቤት ፣ እስረኞች ኮ/ል ደመቀ ተላልፎ ሊሰጥ አይገባውም በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ ፖሊሶች በወሰዱት እርምጃ በርካታ እስረኞች መጎዳታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ወረዳ እና ቀበሌዎች ህዝቡ አስተዳደሩን መስማት አቁሟል። በሰሜን ጎንደር ደምብያ ፤ ዳባት ፤ ቆላ ድባ እና በሰሜን ሽዋ ዞን በሚገኙ ሲዳብርና ዋዩ ፤ደነባ ፣ ማጀቴ ፣ ዓለም ከተማ መንግስታዊ አስተዳደር የለም በሚባልበት ደረጃ ተደርሷል።