የውሃ አጠቃቀም ችግር በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 18 ፥ 2008)

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚታየው የውሃ አያያዝ ችግር በህዝቡ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተገለጸ።

በውሃ አያያዝ ችግር የሚከሰተው ድርቅና ጎርፍ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ሄለን ፓርከት የተባሉ የወተር ኤይድ የስትራቴጂ ባለሙያ በሮይተርስ ድረገጽ ላይ ባወጡት ጥናታዊ ጽሁፍ ገልጸዋል።

በዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመከሰቱ ከ10 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን አዝመራ እንደወደመባቸው የገለጹት ሄለን ፓርከር፣ ችግሩ የተከሰተው በውሃ አያያዝ ጉድለት እንደሆነ በሮይተርስ ድረገጽ ላይ አስፍረዋል። በውሃ ሃብት አያያዝ ችግር ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ በመከሰቱ 100 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ300,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን በዚሁ ጹሁፍ አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የሚታየውን የውሃ ሃብት አያያዝ ጉድለት ካላሻሻለች ወደፊትም ከዚህ የባሰ ዕጣ እንደሚገጥማት የተናገሩት የውሃ ሃብት ባለሙያ ሚስ ሄለን ፓርከር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት የግጦሽ ሳር በማታጣቸው ለሞት መዳረጋቸውን በጹሁፋቸው አስፍረዋል።

አዝመራ በድርቅና በጎርፍ ሲወድም የቤተሰብ ሃላፊዎች ቀሪ ንብረቶቻቸውን እየሸጡ ወደ ሌሎች  አካባቢዎች በመሄዳቸው ማህበራዊ ቀውስ እንደተፈጠረ በጹሁፋቸው አትተዋል።

ኢትዮጵያ በወንዞቿ ላይ ግድብ በመገንባት እና የተጠራቀመውን ውሃ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በማሰራጨት የውሃ ፍሰቷን መቆጣጠር እንዳለባት የገለጹት የውሃ ሃብት በለሙያዋ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ ላይ ቁጥጥር ካላደረገች በህዝቧ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል መታወቅ አለበት ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የውሃ ሃብት አያያዝ ጉድለት በተለይም በአነስተኛ የግል ዕርሻዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ የገለጹት የውሃ ሃብት ባለሙያዋ፣  በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ የሚሆኑት በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ቦታ የሚገኙ ድሃ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቂ ውሃ እንደማያገኙ የገለጹት ሚስ ፓርከር፣ በገጠር የሚኖሩ ዜጎች ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ በመጓዝ ጊዜያቸውን እንደሚያጠፉ አብራርተዋል። ይህም በሴቶችና በህጻናት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አምጥቷል ሲሉ በጹህፋቸው አስፍረዋል።

በላይኛው እና በታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የውሃ ሽሚያ ውስጥ እንደገቡ የተናገሩት የውሃ ሃብት ባለሙያዋ፣ የውሃ ሃብቱ እቅድ ወጥቶለት ፍትሃዊ ስርጭት ካልተደረገ፣ በድሃው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ተገልጿል።

ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰው ቀውስ ለመውጣት ረጅም ፈተና እንሚጠብቃትም ባለሙያዋ ገልጸዋል።