ኢሳት (ነሃሴ 19 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ክልል በተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባቱ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል በፍጥነት እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ ማዕበል የፌዴራል እና የክልሉ ባለስልጣናት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው የኢሳት የውስጥ ምንጮች ገለጸዋል።
በሰሜን ጎንደር፣ አላፋ ጣቁሳ፣ ደንቢያ፣ ጮሂት፣ ጎርጎራ፣ ደባርቅ፣ ዳባት፣ አምባ ጊዮርጊስ እንዲሁም በባህርዳር፣ ፍኖተሰላም፣ ደብረማርቆስና ሌሎች አካባቢዎች የተዛመተው ህዝባዊ እምቢተኝነት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በተደጋጋሚ መግለጫ እንዲያወጣና እንዲያስፈራራ መገደዱን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ያሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለቀናት የተቀመጡበትን የኢህአዴግ ም/ቤት ግምገማ አቋርጠው ህዝቡን ለማስፈራራት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ገዱ፣ “በአማራ ክልል ያለው ሁከትና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግስት አይፈቅድም፣ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” ቢሉም ህዝቡ ቁጣውን ለማሳየት እምቢተኝነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በክልሉ ፕሬዚዳንት መግለጫ ላይ እንዲሁም በህዝባዊ ትግሉ ዙሪያ ከሰሜን ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስና ፍኖተሰላም አስተያየታቸውን ለኢሳት የሰጡት ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የክልሉ ፕሬዚደንት መግለጫ ጭንቀት የወለደውና አመጹን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
የመንግስት የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎችን አምኖ ተቀብሎ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ እርምጃ እወስዳለሁ ለዚህም ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ ማለቱ በጣም እንዳስቆጣቸውና የበለጠ ለትግሉ እንደሚያነሳሳቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን ወደ ሌላ ቦታ አዛወርናቸው ማለታቸውን መንግስትና አስተዳደሩ ፈልጎ የፈጸመው ሳይሆን የህዝቡ ትግል የፈጠረበት ጫና እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።