ኢሳት (ነሃሴ 19 ፥ 2008)
የአለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ማጠናቀቂያ ወቅት ላሳየው የፖለቲካ ተቃውሞ የሚወስደው እርምጃ እንደሌለ ማረጋገጡ ታወቀ።
የቢቢሲ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ከኮሚቴው የተገኘው ማላሽን ዋቢ በማድረግ በአትሌቱ ላይ የተካሄደ ምርመራ መዘጋጀቱንና የሚወስድ እርምጃ አለመኖሩ አመልክቷል።
አትሌቱ በወቅቱ ያስተላለፈው ፖለቲካዊ መልዕክት ከኦሎምፒክ ህግጋት ጋር የሚጻረር ሊሆን ይችላል በማለት የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጉዳዩን እንደሚመለከተው መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና የአትሌቱን ድርጊት ሲመረምር የሰነበተው ኮሚቴው በአትሌቱ ላይ የሚወስደው ዕርምጃ እንደሌለ ማረጋገጡን ከቢቢሲ ስፖርት ለመረዳት ተችሏል።
ለዜና አውታሩ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ከሪዮ ዴ ጄኔሮ ቃለምልልስን የሰጠነው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በበኩሉ ኢትዮጵያውያን እያደረጉለት ባለው ድጋፍ እጅት ደስተኛ መሆኑን አስታውቋል።
የህግ አካላት አትሌቱ ወዳለበት ከተማ በማቅናት ላቀረበው የፖለቲካ ጥገኝነት ሙያዊ ምክርን እና አገልግሎትን እየሰጡ እንደሆነም ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።