ኢሳት (ነሃሴ 18 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን በውጭ ሃገር የስራ ተቋራጮች ለማካሄድ በቅርቡ የተላለፈ ውሳኔ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ እንዲቋረጥ ተደረገ።
በከተማዋ ያለውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ ሲባል መንግስት አለም አቀፍ የኮንስትራሽን ኩባንያዎች በግንባታው ዘርፍ እንዲሰማሩ ባለፈው አመት ውሳኔ ማስተላለፉና አለም አቀፍ ጨረታ መውጣቱ ይታወሳል።
የጨረታውን መውጣት ተከትሎ ከተለያዩ ሃገራት የተውጣቱ 28 ኩባንያዎች ተሳትፈው 14ቱ ብቁ መሆናቸው ታምኖበት ስራው እንዲሰጣቸው ለውሳኔ ቀርቦ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ የሚገኘው መንግስት በክፍያ አፈጻጸም ዙሪያ ላይ ውሳኔ ላይ መድረስ ባለመቻሉ እቅዱ ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጄክት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዮሴፍ ብሩ ከኩባንያዎቹ ክፍያ የሚፈጽመው በውጭ ምንዛሪ ከሆነ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ላይ ጫና አይፈጥርም ወደ ሚለው አበይት ጉዳይ በመንግስት በኩል ውሳኔ እንዳላገኘ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ለግንባታ የተመረጡት 14 አለም አቀፍ የግንባታ ተቋራጮች የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘው ቢመጡ አከፋፈሉ በምን መንገድ መከናወን እንዳለበት እልባትን ሊያገኝ አለመቻሉ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ቢያዝም ግንባታው በሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ በሚል መንግስት ባለፈው አመት አንድ ተቋምን በማቋቋም የውጭ ሃገር ኩባንያዎችን ተሳታፊ ለማድረግ ቢጥርም በሃገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንቅፋት መፍጠሩን ለመረዳት ተችሏል።
በመዲናይቱ አዲስ አበባ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ቤት ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ሲሆኑ፣ የውጭ ኩባንያዎችን ለማሳተፍ ተይዞ የነበረው ሄደት እንዲቆም መደረጉ ችግሩን ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።
በከተማዋ ከ12 አመት በፊት የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለማግኘት ተመዝግበው የነበሩ ነዋሪዎች አሁንም ድረስ በእጣ ቤት መግኘት እንዳልቻሉ በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከኢገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።