በአማራ ክልል የሚደረገው የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ አድማሱን እያሰፋ ነው

ነሃሴ  ፲፯ ( አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባህርዳርን ለሶስት ቀናት ጸጥ ረጭ ያደረገው የስራ መቆም እና ከቤት ያለመውጣት አድማ ወደ ደባርቅ፣ ቆላ ድባ፣ ጯሂትና ጎርጎራ ከተሞች ተሸጋግሮ በጸጥታ ሃይሎችና በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። በገበያው ውስጥ ምንም እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የገበያው ዋና ዋና በሮች ተዘግተው በገበያው ጠባቂዎች ይጠበቃሉ፡፡በተለይ ከአስራ አንድ ሰዓት በኋላ  ግርግር የሚበዛባቸው የገበያው በሮችና የእግረኛ መንገዶች ምንም አይነት ውክቢያም ሆነ እንቅስቃሴ  አይታይባቸውም፡፡ ሁሉም የባህርዳር ነዋሪዎች የህዝባዊ እምቢተኝነቱ አካል የሆነውን የስራ ማቆም አድማ በሙሉ ልቡ ተቀብለው ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡

ዘጋቢያችን እንዳለው ዛሬ ማክሰኞ  በከተማዋ የታየው ለየት ያለ ተግባር የስርዓቱ ወታደሮች ከሁለት ሳምንት በፊት በንጹሃን ላይ በወሰዱት የግፍ ግድያ ጓደኞቻቸውን ያጡ ወጣቶች በቡድን በመደራጀት  በስራ ማቆም አድማው ያልተሳተፉትን ተሸከርካሪዎች ለማስቆም መሞከራቸው ነው፡፡በተለይ በቀበሌ አስራ ሁለት አካባቢ የተሰማሩት ወጣቶች አንድ በተለምዶ ʻአባዱላʼ በሚል የሚጠራ ተሸከርካሪ እንዲመለስ ሲያስጠነቅቁ ፣ ጥሶ ለማለፍ በመሞከሩ የፊት መስታውቱን በመምታት ርምጃ ወስደዋል፡፡ በትላንትናው ምሽትም ቀን ሲሰሩ በዋሉ ባጃጆች ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ፤የገዥው መንግስት አመራሮች የማይሰሩ ባጃጆችን እንቀጣለን በማለት ሲያስፈራሩ ቆይተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የግል ባንኮች ጠዋት አገልግሎት ለመጀመር ፈራ ተባ በማለት በራቸውን በከፊል በመክፈት ስራ ለመጀመር ቢሞክሩም ተጠቃሚ አላገኙም፡፡ከአምስት ሰዓት በኋላም ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ስራ አቁመዋል፡፡ዛሬም የተለያዩ መስሪያ ቤቶች በራቸውን ክፍት ቢያደርጉም ከተወሰኑ ኃላፊዎች ውጭ ሰራተኛው እንዳልተገኘ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ፖስታ ቤት ዛሬም አገልግሎት አልሰጠም፡፡ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ከአውቶቡስ መናኸሪያ በስተጀርባ የሚገኙ ʻሽሮ ቤቶችʼና አልፎ አልፎ ሙዝና ብርቱካን የሚነግዱ ኮንቴይነሮች  ብቻ ናቸው፡፡

በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ አባት ለዘጋቢያችን አንደተናገሩት በከተማዋ የሚደረገውን ትግል አባቶችና አዛውንቶች ሊያግዙ ይገባል።

‹‹በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄደው ትግል አባቶችም ተሳታፊ ልንሆን ይገባል፡፡አሁን የስርዓቱ ማንነት ተጋልጧል፡፡ከዚህ በኋላ ወደፊት እንጅ ወደኋላ ማለት አይገባም፡፡ቁርስ ምሳና እራት እንበላ እንደሆን ምሳ ብቻ በመብላት ከህዝብ ጋራ መተባበር አለብን፡፡ህዝቡም በየአካባቢው የሚገኙትን ሰርቶ አዳሪዎች መደጎምና ማገዝ እንጅ ፤የስራ ማቆሙ አድማ እንዲቆም የሚቀሰቅሱ የህውሃት አደርባይ አመራሮችን ድምጽ መስማት የለብንም፡፡ ሁሉም አንድ ከሆነ እኮ ሊወሰድ የሚችል አንድም እርምጃ አይኖርም›› በማለት በወቅታዊው ሁኔታ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

መስተዳድሩ በንግድ ድርጅቶች በሮች ላይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በማለት ወረቀቶችን እየለጠፈ ቢሆንም፣ ነጋዴዎች ለማስፈራሪያው ቦታ አልሰጡም። መስተዳድሩ በንግድ ድርጅቶች ላይ ቅጣት የሚጥል ከሆነ እርምጃው ከዚህ በከፋ ሁኔታ እንደሚቀጥል ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በደባርቅ ዛሬ በተጀመረው የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ ደግሞ ፣ የገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች ነጋዴዎች በግዴታ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ለማስገደድ ሲሞክሩ፣ ከህዝብ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባታቸው ሁለት ታጣቂዎች በድንጋይ ተመትተው ሆስፒታል ሲገቡ ከሲቪሉ ወገን ደግሞ ሶስት ሰዎች ተጎድተዋል። የከተማው ህዝብ በአንድ ድምጽ በወሰደው እርምጃ፣ ወደ አካባቢው የሚንቀሳቀስ ተሽካርካሪ ቆሟል። በከተማው ውስጥ ተከታታይ የተኩስ ድምጾች እየተሰሙ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በቆላ ድባ፣ ጫሂትና ጎርጎራ ከተሞች የሚደረገው አድማ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን፣ በቆላ ድባ ሁለት ወጣቶች መታሰራቸውን ተከትሎ ህዝቡ በአንድነት በመሄድ እንዲፈቱ አድርጓል። በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪም ሆነ የተከፈተ የንግድ ድርጅት እንደሌለ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጎንደርም ተመሳሳይ አድማ ለ2ኛ ጊዜ እንዲጀመር የሚጠይቅ ወረቀት እየተበተነ ነው። ህዝቡ ለተከታታይ ቀናት የሚያቆየውን ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲገዛ ተጠይቋል።