ነሃሴ ፲፯ ( አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በታላቁ የሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በመላው ዓለም ባሉ የመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛውን የዜና ሽፋን አግኝቷል።
የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ማሳየቱን ተከትሎ በተለይ በአገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝቡ መነጋገሪያ ዋና ጉዳይ ሆኗል። ገዥው ህወሃት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያደርሰውን የጅምላ ግድያ፣ እስራትና ማፈናቀል በመቃወም እጁን አጣምሮ በመግባት የትግሉ አጋርነቱን ያሳየውና በመላው ዓለም አፈናውን እንዲታወቅ ላደረገው አስተዋጾ ከፍተኛ አድናቆቶች እየጎረፉለት ነው። በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አትሌት ፈይሳን በሞራልና በገንዘብ በማገዝ ወገንተኝነታቸውን እያሳዩት ሲሆን እስካሁንኗ ሰዓት ድረስ ከ77 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ መዋጮ ተሰብስቧል።
ታላላቆቹ የዜና አውታሮች ቢቢሲ፣ ፎክስ ኒውስ፣ ሲኤንኤን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ና ስካይ ኒውስን ጨምሮ ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች የፈይሳ ሌሊሳን ዜና ትኩረት ሰጥተው ዘግበውታል።