በባህር ዳር ከቤት ያለመውጣት አድማ ለሶስተኛ ቀን በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ

ኢሳት (ነሃሴ 17 ፥ 2008)

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እሁድ በነዋሪው የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ እንዲያበቃ ቅስቀሳንና ዛቻን ቢያደርግም አድማው ማክሰኞ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

ከተማዋ ማክሰኞች ምሽት ድረስ ሙሉ ለሙሉ ከማኛውም እንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏን የተናገሩት እማኞች የባህር ዳር ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ የንግድ ተቋማት ስራቸውን እንደሚጀምሩ ማሳሰቢያዎችን ቢያሰራጭም ነዋሪው እምቢተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ለሶስት ቀን እንዲካሄድ የተጠራው ከቤት ያለመውጣት አድማ ማክሰኞች ያበቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎች መንግስት ይፈጽመዋል ያሉትን ግድያና አፈና ለመቃወም የተለያዩ ዕርምጃዎችን በቀጣይ እንደሚወስዱ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የከተማዋ አስተዳደር ነዋሪው የንግድ ድርጅቱን እንዲከፍት ማሳሰቢያዎችን በተደጋጋሚ ቢያሰራጭም የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ለሶስተኛ ቀን ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ሆነው መዋላቸው ታውቋል።

በከተማዋ በቅርቡ የተፈጸሙ ግድያዎችን በመቃወም የባህርዳር ከተማ በራሱ ተነሳሽነት ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ እሁድ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ አድማ ውስጥ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ሲካሄድ የቆየው አድማ የተሳካ እንደነበር አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች አድማው የህዝቡ ጥያቄ ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ በተለያዩ ስልቶች ቀጣይ እንደሚሆን አክለው አስታውቀዋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባትን እንዲያገኝና እየተፈጸመ ያለው ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ዙሪያ የተነሳው ህዝባዊ ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ተቃውሞ እየቀረበ ይገኛል።