ነሃሴ ፲፮ ( አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰቆጣ ከተማ በእያመቱ የሚከበረውን የሸደይ በአል ለማክበር የፌደራል እና የክልል መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ሳይገኙ ቀርተዋል።
በአሉ በእያመቱ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በበአሉ ላይ እየተገኙ ንግግር የማድረግ ልማድ ቢኖራቸውም፣ በዘንድሮው በአል ላይ ግን አልተገኙም።
ባለስልጣናቱ በበአሉ ላይ ለመገኘት ለምን እንዳልፈለጉ ባይታወቅም አንዳንድ ወገኖች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታው ውጥረት እንዳይገኙ እንዳደረጋቸው አስተያየት ይሰጣሉ።
የከተማዋ ወጣቶች የባለስልጣናቱን መምጣት ተከትሎ ተቃውሞ ያነሳሉ የሚል መረጃ መሰራጨቱም ለባለስልጣናቱ መቅረት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
የብአዴን መሰረት ነው የሚባለው የዋግ ህምራ ዞን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ቅሬታውን እያሰማ ነው። አበርገሌ በሚባለው አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ከወርቅ ማእድን ማውጣት ጋር በተያያዘ እኛ ተጠቃሚዎች አይደለንም በሚል ተቃውሞ አድርገው በጸጥታ ሃይሎእ እንዲታፈን ተደርጓል።