ነሃሴ ፲፫ ( አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአየር ሃይል ምንጮች እንደገለጹት ከኢታማዦች ሹሙ በተሰጠ ትእዛዝ መሰረት የህወሃት አባላት የሆኑ የአየር ሃይል አባላት ተንቤን በሚከበረው የአሸንዳ በአል ላይ እንዲገኙ በሚል ሰበብ ወደ ትግራይ እንዲሄዱ ታዘዋል።
ነሃሴ 9 ቀን 2008 ዓም የተጻፈውን ደብዳቤ ተንተርሶ የአየር ሃይል አባላቱ ወደ ትግራይ የተጓዙ ሲሆን፣ ስለወቅቱ ሁኔታ መመሪያ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሸንዳ በአል ሰበብ አድርጎ ሁሉም የህወሃት አባላት ተመርጠው እንዲሁ መደረጉ በአየር ሃይል ውስጥ ቅሬታና እና ጥርጣሬ ፈጥሮአል። ድርጊቱ በሰራዊቱ መካከል ያለውን አለመተማመን እንዲጨምር አድርጎታል።
በባህርዳር እና አካባቢው በሚገኘው የምዕራብ እዝ አብዛኛው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሚወሰደው እርምጃ ተቃውሞ እያሰሙ በመምጣታቸው ታማኝ የሰራዊት አባላት ብቻ ተመርጠው ጥበቃ እያደረጉ መሆኑም ታውቋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ሃይቅ ከተማ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑ 9 ሰዎች ሲታሰሩ የንግድ ሙዚቃ ቤት ባለቤት የፋሲል ደሞዝን ሙዚቃ በድምጽ ማጉያ አሰምተሃል በሚል ሲታሰር፣ በተለያዩ ሰበቦች በአካባቢው የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር ከመቶ በላይ ደርሷል። በደሴ፣ ኮምቦልቻና አካባቢዋ እንዲሁም በሰሜን ወሎ በወልድያና አካባቢው በርካታ ወጣቶች ታስረው ይገኛሉ። ገዢው ፓርቲ አካባቢውን ወታደራዊ ቀጠና በማስመሰል፣ ህዝቡን አፍኖ ለመግዛት መቁረጡን ነዋሪዎች ይናገራሉ።