ነሃሴ ፲፩ ( አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነሃሴ 11 ቀን 2008 ዓም በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስም በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የክፍለ ከተማ አመራሮች ስብሰባ የተጠሩ ቢሆንም፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት የህውሃት አመራሮች ሆነው መገኘታቸው ውዝግብ አስነስቷል።
ሰብሳቢው “ በወልቃይት ላይ የሚነሳው የአማራነት ጥያቄ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑንና ጉዳዩን ሊመለከቱት የሚገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የክልል አንድ አመራሮች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጉዳዩን ረስቶ የሚረጋጋበትን መንገድ መፈለግ ከሁሉም አመራር ይጠበቃል “ የሚል መልእክት እያስተላለፉ ባለበት ወቅት፣ በባለስልጣኑ ንግግር የተበሳጩት ተሰብሳቢዎች በጩኸትና ፉጨት ንግግሩ እንዲቋረጥ አድርገዋል።
የክልሉ ህዝብም ሆነ አመራሩ የህውሃት ፕሮፖጋንዳ እንደበቃው የታየበት ስብሰባ እንደነበር የገለጹት የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ‹‹ ስብሰባውን ለምን በአቶ ገዱ ስም ተጠራ ?በእሳቸው ስም ከተጠራስ ርዕሰ መስተዳድሩ የት ናቸው? ›› በማለት ከአዲስ አበባ መጥተው ስብሰባውን የመሩትን የህውሃት ባለስልጣን በጥያቄ አፋጠዋል።
አቶ ገዱ ስብሰባውን እንዲጠራ ማድረጋቸውን የገለጹት ባለስልጣኑ ‹‹እኛም እንደ እናንተ በወልቃይት ጥያቄ ዙሪያ ውስጣችን አሯል!›› በማለት የክፍለ ከተማ አመራሮችን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ፣ አመራሮቹ ግን ተቃውሞአቸውን ደጋግመው በጩኸትና በፉጨት በመግለጽ ሳይቀበሉዋቸው ቀርቷል።
ሰሞኑን የባህርዳር ከተማ የልዩ ልዩ መስሪያ ቤት አመራሮችን፣ የየመስሪያ ቤቱ የስራ ሂደት ኃላፊዎችንና በዙሪያ ወረዳ የሚገኙ የሁሉም ጽህፈት ቤት አመራሮችንና አስተዳዳሪዎችን በመሰብሰብ በወልቃይት ዙሪያ የተነሳውን ህዘባዊ እንቅስቃሴ ለማክሰም ሙከራ ቢደረግም፣ ታች ያሉ አመራሮች ግን ‹‹ወንድሞቻችንን ተገድለዋል፤የብአዴን አመራርም በዝምታ እያየ ነው፤አሁንም የሕውሃት አገዛዝ ይብቃ ያለን ህዝብ እንዴት እናስቆመዋለን? ባዶ እጁን የወጣውን ህብረተሰብ የገደሉ የአጋዚ ወታደሮች ለምን በንጹሃን ላይ እንደተኮሱ አይጠየቁም?…››የሚሉ ጥያቄዎችን በማቅረብ በታላቅ ድፍረት ጥያቄዎችን በማቅረብ፣ የላይ አመራሩ የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም።
በአማራ ክልል የሚገኙ አብዛኛው የብአዴን አመራሮችና አባላት ሰሞኑ በተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ እንደሚደግፉት በተዘዋዋሪ ሲናገሩ መሰማታቸው ለህውሃት ስርዓት አልገዛም ባይነቱ በብአዴን ዘንድም እየጎላ መምጣቱን ተሰብሳቢዎች ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በክረምቱ መርሃ ግብር የሚማሩ የትግራይ ተወላጆች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ እያደረገ ነው። የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪዎቹ በትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ገብተው እንዲማሩ ለማድረግ ማቀዱን ምንጮች ገልጸዋል። ተማሪዎቹ የአየር ትኬት ተገዝቶላቸው ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ ከዛም ወደ መቀሌ እንዲሄዱ እየተደረገ ነው። በጎንደር ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ እንዲወጡ ተደርጓል።
ህወሃት ሆን ብሎ ህዝባዊ ተቃውሞውን የብሄር ግጭት ያለ ለማስመሰል የሚሄድበት እርቀት ትችት እያስከተለበት ነው።