በምስራቅ ሸዋ ሆራ ፈጀሶ የተባለ ወጣት አንድ የአጋዚ ወታደር ገድሎ ሌላ አንድ የፌደራል ፖሊስ ካቆሰለ በሁዋላ ተገደለ።

ነሃሴ  ፲፩ ( አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሌሊቱ 10 ሰአት ላይ ወታደሮቹ  “የጦር መሳሪያ አለህና አውጣ” ብለው  የቤቱን በር በሃይል ሰብረው ሲገቡ፣ ወጣት ሆራ እጄንማ አልሰጥም ብሎ አንዱን ግንባሩ ላይ በሽጉጥ መትቶ ሲገድለው፣ ሌላውን ደግሞ ሆዱ አካባቢ መትቶ ጥሎታል። የአጋዚው ወታደር ወዲያኑ ህይወቱ ሲያልፍ፣ የፖሊስ አባሉ ደግሞ ሆስፒታል ገብቷል። በዚህ የተበሳጩት ወታደሮች ወጣቱን ከገደሉት በሁዋላ በአስከሬኑ ላይ ደጋግመው በመተኮስ ንዴታቸውን ለመወጣት ሞክረዋል። ባለቤቱና የአንድ አመት ልጁም ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

የከተማው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ የሆነው ከድር ገመዳ፣ ወጣት ሆራ የጦር መሳሪያ ያለው እና መንግስትን የሚቃወም መሆኑን በመጠቆም ሊያስይዘው ቢሞክርም ወጣቱ ግን እጄን ለእናንተ አልሰጥም በሚል ተኩስ በመክፈት እርምጃ ወስዷል።

በወጣቱ ላይ የተተኮሰው የጥይት ብዛት አስገራሚ ነው የሚሉት የአይን እማኞች ፣ ወጣቱ ከተገደለ በሁዋላ አስከሬኑ መጎተቱን ባለቤቱም መደብደቡዋን ተናግረዋል ።

“የከተማው ነዋሪዎች ተቃውመንም ዝም ብለንም መገደላችን አልቀረም፣ ወያኔ ብዙ አመት ከፋፍሎ ገዝቶናል እባካችሁ በአንድነት እንነሳ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።”

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ በኦሮሚያ ክልል በመንግስት የሚፈጸመው ወታደራዊ የሽብር ተግባር ተባባሶ መቀጠሉን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በጣሰ መልኩ በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ ተባብሶ መቀጠሉንና አፋጣኝ እልባት ሊበጅለት እንደሚገባ ሊጉ በሪፖርቱ ጠቁሟል።

የአጋዚ ወታደሮች ኦገስት 6 ቀን 2016 የሕክምና  ባለሙያ የሆኑትን ዶክተር ገበየሁ ጃለታን በግፍ በጥይት መምታታቸውን የገለጸው ሊጉ፣  ዶ/ሩ በነቀምት ከተማ የግል ክሊኒክ ባለቤት ሆነው ሲሰሩ  በአጋዚ ታጣቂዎች በጥይት ተመተው የሚመጡ ቁስለኞችን በማከም አስተዋጾ ሲያደርጉ እንደነበሩ ገልጿል። ዶክተር ገበየሁ ጃለታ በወቅቱ በጥይት ተመትተው ነቀምት ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው የቆዩ ቢሆን ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

በቅርቡ ከኦገስት 6 ቀን 2016 ጀምሮ በተካሄደው የመላው ኦሮሚያ ሕዝባዊ አመጽ ላይ ብቻ ቁጥራቸው ከ70 በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ተገለዋል። በሽዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች በጅምላ ታስረው ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይገኛል። በአጠቃላይ የኦሮሚያ ሕዝባዊ ማእበል ከተጀመረ ከኖቨምበር ወር 2015  ጀምሮ በመላው ኦሮሚያ ክልል የተገደሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ቁጥር ከ700 በላይ መድረሱን  የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ በሪፖርቱ አመላክቷል።

በምስራቅ ሃረርጌ ዞን በአወዳይ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት፣ በምእራብ አርሲ ዞን አዳባና ዶዶላ፣ በባሌ፣ በአዲስ አበባ፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማና ዝዋይ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ  ሰላማዊ ዜጎች ተገለዋል። ወደ እስር ቤትም በገፍ ተወስደው ታሰረዋል። ኦገስት 6 ቀን 2016 የተገደሉትን ቁጥራቸው 65 የሚሆኑትን ስምና አድራሻቸውንና ጨምሮ በምስል የተደገፈ መረጃ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ ይዞ ወጥቷል።

በኦሮሚያ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲሰየም ሲል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ ጥያቄ አቅርቧል።