በኢትዮጵዊያን ላይ የሚፈጸመውን ግድያ የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች እየተደረጉ ነው

ነሃሴ  ፲፩ ( አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአውሮፓና አሜሪካ የተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የህወሃት ኢህዴግን የጅምላ ግድያና እስራት በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፎች እያደረጉ ነው። በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በተደረገ የሰላማዊ ሰልፍ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ መተኮስ ወንጀል ነው፣ በደም የወጣ ስልጣን አይቆምም፣ ዘረኛ መንግስት ዘረኛ ነው፣ የመሬት ወረራው ይቁም፣ የሚሉ መፈክሮችን ተሰምተዋል።

በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በበኩላቸው የዘር ማጥፋት ግድያ ይቁም፣ ዘረኝነት ይብቃ፣ የኦሮሞና አማራ ብሔር ተወላጆች ግድያ ይቁም፣ የኮሪያ መንግስት አንባገነኑን የኢትዮጵያ መንግስት በገንዘብ ማገዙን ያቁም፣ የህወሃት የበላይነት ያብቃ፣ የፓለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ይፈቱ የሚሉ መፈክሮችን በማንገብ በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ፈትለፊት ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።

በተመሳሳይም የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝን በመቃወም በአውሮፓ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው ቤልጅየም አርብ ኦገስት 19 ቀን 2016 የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል።  በተመሳሳይም ኦገስት 19 ቀን 2016 በሆላንድ ደንሃግ የሆላንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ፊት ለፊት እንዲሁም በስዊድን ስቶክሆልም እና  በኖርዌይ ኦስሎ ላይ የተቃውሞ ሰልፎች መጠራታቸውን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።