ኢሳት (ነሃሴ 11 ፥ 2008)
ሰሞኑን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ለማሰብ ረቡዕ ምሽት በጎንደር ከተማ ሊካሄድ የነበረውን ልዩ የፀሎትና የሻማ ማብራት ስነስርዓት ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መስተጓጎሉን ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።
ላለፉት ሶስት ቀናት ከቤት ባለመውጣት አድማ ውስጥ የቆዩት የከተማዋ ነዋሪዎች ዝግጅቱን ለመታደም ወደ አደባባይ ቢወጡም ከጸጥታ ሃይሎች ጋር አለመግባባት መፈጠሩን እማኞች አስረድተዋል።
በከተማዋ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና ልዩ ሃይል ተሰማርቶ እንደሚገኝ የተናገሩት እማኞች ነዋሪዎች ሃዘናቸውን ለመግለጽ በመስቀል አደባባይ ቢገኙም የጸጥታ ሃይሎች ዝግጁትን ለመበተን ሙከራ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
የጸጥታ ሃይሎች ሊወስዱ የነበረውን እርምጃ ተከትሎ በስፍራው በተገኙ ነዋሪዎች በጸጥታ ሃይሎች መካከል አለመግባባት መፈጥሩንና ዝግጅቱ ሊስተጓጎል መቻሉን ለመረዳት ተችሏል።
የጸጥታ ሃይሎች ድርጊት ቅሬታ ያደረባቸው ነዋሪዎች የጀመሩትን ትግል በሰላማዊ መንገድ ለመቀጠል ርብርብ እያደረጉ መሆኑንም አክለው አስታውቀዋል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ሻማዎችን በመያዝ በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ድርጊት በማውገዝ የተለያዩ መፈክሮችን ሲያሰሙ ማምሸታቸውንም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በተያያዘ ሁኔታም ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆነ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን በማሰብ ረቡዕ የጸሎት ፍታት አካሄደዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ማክሰኞ በሁለቱ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በማውገዝ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እዳካሄዱ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
እንዲሁም በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ዝግጅት ማካሄዳቸውን ተባባሪ ባልደርባችን ንግስት ሰልፉ ከስፍራው ዘግባለች።
ከቀጣይ ቀናቶች በተለያዩ ሃገራት የሚከናወኑ ዝግጅቶችም እንዳሉ ለኢሳት እየደረሱ ያሉ መረጃዎች አመልክቷል።