የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን አስታወቁ

ኢሳት (ነሃሴ 10 ፥ 2008)

በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን ያካሄዱ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ መጀመራቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

የከተማዋ ነዋሪዎች ማከሰኞ ጠዋት ከዞንና ከከተማው አስተዳደር ሃላፊዎች ጋር ምክክርን በማካሄድ ለእስር የተዳረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።

ነዋሪዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ የስራ ማቆም አድማ እንደሚጀምሩ ለሃላፊዎቹ በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውንና ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ነዋሪው የንግድ ድርጅቶችን ሙሉ ለሙሉ መዝጋቱን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ቅዳሜ ያካሄዱትን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በርካታ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

በከተማዋ የሚገኙ የጸጥታ አባላት የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ትምህርት ቤቶችንና የሲኒማ ቤቶችን በጊዜያዊ እስር ቤትነት እየተጠቀሙ መሆኑን እማኞች አስረድተዋል።

እነዚሁ እስረኞች እንዲፈቱ ጥያቄን በማቅረብ ላይ ያሉት ነዋሪዎች ህዝቡ ያነሳውን ሰላማዊ ጥያቄ አግባብ ያለው ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ የስራ ማቆም አድማው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በሃላፊዎችና በነዋሪው መካከል ማክሰኞ ጠዋት የተካሄደው ውይይት ያለስምምነት መበተኑን የተናገሩት እማኞች ቅዳሜ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ህገወጥ ብሎ በመንግስት መፈረጁን ቁጣ እንደቀሰቀሰ አክለው አስረድተዋል።

ከቅዳሜ ጀምሮ ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዙ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችም አሁንም ድረስ ስራ አቁመው እንደሚገኝ ነዋሪዎች አከለው አስታውቀዋል።

በከተማዋ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የተጀመረውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የንግድ ተቋማትን ጨምሮ የትራስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ታውቋል።

ላለፉት ሶስት ቀናቶች የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከቤት ያለመዉጣት ተቃውሞ ሲያካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ  በጸጥታ ሃይሎች ለተገደሉ ሰዎች ሻማ የማብራት ስነስርዓት እንደሚያካሄዱ ለኢሳት የደረሰ መረጃ ያመለክታል።