በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ህወሃት ኢህአዴግ ከስልጣን ተወግዶ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠየቁ

ኢሳት (ነሃሴ 9 ፥ 2008)

በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የህወሃት ኢህአዴግ መንግስት ከስልጣን ተወግዶ በምትኩ ከፖለቲካ ድርጅቶች ሲቪክ ማህበራትና ብቃት ካላቸው ግለሰቦች የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም መግለጫ አወጡ።

“ለ25 አመታት ሙሉ ህዝባችንን አፍኖ ሲገዛ የቆየና ለ40 አመታት ሰላማዊ ዜጎችን እየረሸኑ አገራችንን እየዘረፉ የቆዩ ባልስልጣኞች ያሉበት ህወሃት/ኢህአዴግ በተለይ በዚህ አመት በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች ላይ ጦርነት ከፍቷል። የአገዛዙን የግድያ ወንጀሎች እናውግዛለን፣ የህዝቡንም ተቃውሞ እንደግፋለን” በሚል መንደርደሪያ መግለጫውን ያወጡት የትግራይ ተወላጆች፣ ለአላማው መሳካት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችው እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

እነዚህ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ህወሃት/ኢህአዴግን ከስልጣን ለማስወገድና ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ለመመስረት እንዲያስችል ባለ አምስት ነጥብ የትግል ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ ፋታ ሳይሰጥ አፋኙን አገዛዝ እንደሚያስወግድ ፥ በሰላዊ ህዝብ ውስጥ የእርስ በእርስ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ ሰራዊቱና ሌሎች የመንግስት ታጣቂዎች በህዝባቸው ላይ እንዳይተኩሱ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ የትግራይ ህዝብ በራሱ ላይ ብዙ ግፍ የሚፈጸመውንና በስሙ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የሚጨፈጭፈውን ህወሃት አውግዞ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት የትግል  ጥሪዎች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ውጭ ነጻነት ባላቸው አገሮች ውስጥ እየኖሩ የግፍ ስርዓቱን ዕድሜ ለማራዘም የሚሞክሩ ግለሰቦች በተለይም የህወሃት ደጋፊዎች አደብ ካልገዙ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚፋረዳቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል በማለት አሳስበዋል።