በባህርዳር ከተማ የተገደሉት ሰዎች ከ55 እንደሚበልጡና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁት ዜጎች ታስረው እንደሚገኙ ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 6 ፥ 2008)

ከቀናት በፊት በባርዳር ከተማ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተፈጸመ ግድያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በከተማዋ ብቻ 55 መድረሱንና ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ነዋሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

በሳምንቱ መገባደጃ በባህርዳር እና ጎንደር ከተሞች እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ የገጠር መንደሮች ግድያ ሲፈጸም መቆየቱን ያወሱት እማኞች በሆስፒታል ብቻ 55 ሰዎች አስከሬን ሊገኝ መቻሉን ገልጸዋል።

በርካታ የግድያው ሰለባ የሆኑ ሰዎች አስከሬናቸው ሊለይ ባለመቻሉና ቤተሰቦቻቸው ባለመገኘታቸው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በልዩ ትዕዛዝ እንደቀበራቸው ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በጎንደር ከተማና አካባቢዋ ተመሳሳይ ግድያ የተካሄደ ሲሆን፣ በአካባቢው በአጠቃላይ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለተከታታይ ሶስት ቀናቶች የተካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻሉ።

በግድያው ዙሪያ አለም አቀፍ ገለልገተኛ አካል ማጣራትን እንዲያካሄድ የጠየቀው ተመድ በበኩሉ በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደሆነበት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።