ኢሳት (ነሃሴ 6 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ከሳምንት በፊት ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለሁለተኛ ሳምንት መቀጠሉንና በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ተገለጸ።
ህጻናቶች ሳይቀሩ ለእስር መዳረጋቸውን የሚናገሩት የዞኑ ነዋሪዎች በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ከእስር እንዲፈቱና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚስወዱት ዕርምጃ እንዲቆም በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሎ የሚገኘው ይህንኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ በጸጥታ ሃይሎች ከባድ የአካል ድብደባ የደረሰባቸው እንዳሉም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በሳምንቱ መገባደጃ በዚሁ ዞን ተካሂዶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች መገደላቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
የሃረሪ ክልል ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ጀማል አህመዴ በክልሉ ድሬ ጠያራ ወረዳ በሚገኙ ሶስት አካባቢዎች ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ሃላፊው ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ ጉዳዩ ወደ ህግ አካላት መመራቱን አክለው ተናግረዋል።
የምስራቅ ሃረርጌ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በበኩሉ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
የኮምቦልቻ ወረዳን ጨምሮ በዞኑ ስር በሚገኙት የቀርሳ፣ ፋዲስና ሜታ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ፣ የጸጥታ ሃይሎች ድርጊቱን ለመቆጣጠር እርምጃን እየወሰዱ እንደሆነ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከቀናት በፊት በኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የተካሄዱ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከ100 በላይ ሰዎችን እንደገደሉ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግድያው በገለልተኛ አካል ማጠራት እንዲካሄድበት ጠይቋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ሃሙስ ገልጿል።