በጎንደር በሀገር ሽማግሌዎች ተቃውሞን ለማብረድ እየተካሄዱ ያሉ ድርድሮች በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታን መቀስቀሱ ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 5 ፥ 2008)

በሰሜን ጎንደር ዞን ስር በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት እስከ ሃሙስ ድረስ ስራ አለመጀመራቸውንና በሀገር ሽማግሌዎች ተቃውሞን ለማብረድ እየተካሄዱ ያሉ ድርድሮች በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታን መቀስቀሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።

በዞኑ አለፋ ወረዳ እና አካባቢዋ ያሉ ነዋሪዎች ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በዞሩ ባሉ ወረዳዎች የመንግስት መዋቅሮች ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቆማቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በዞኑ ስር የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች የተቀሰቀሰውን ውጥረት ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት የሃገር ሽማግሌዎችን በማሰማራት ማግባባት እንዲካሄድበት ቢያደርጉም ነዋሪዎች ተቃውሞ ማቅረብ መጀመሩን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ገልጸዋል።

ጎንደር ግድያ እየተፈጸመ እኛ አርፈን አንቀመጥም ሲሉ የተናገሩት ነዋሪዎች የወረዳው ነዋሪ ወልቃይት ድረስ በመጓዝ መብቱን ለማስከበር ቁርጠኝነትን እየገለጸ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ህዝቡን መጠበቅ ባለበት ሰራዊት ግድያ ለምን ይፈጸምብናል ሲሉ ጥያቄን ያቀረቡት የአለፋ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የማግባባት ስራት በማካሄድ ላይ ላሉ የሃገር ሽማግሌዎች የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን እያቀረቡ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ በጎንደር ባህርዳር ከተሞችና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አመራር የሆኑት አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አመራሮች ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ይታወሳል።

ይሁንና የብአዴን አመራሮች ነዋሪውን ለማረጋጋት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርጉም ህዝቡ ተቃውሞ ማቅረቡንና ውይይቱ መስተጓጎሉን መዘገባችን የሚታወቅ ነው።