ነሃሴ ፬ ( አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ መጠየቃቸውን ተክትሎ በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ተክትሎ ላለፍት ሁለት ዓመታት ከየመን ታፍነው የተወሰዱት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸው ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሪፕሪቭ አስታውቋል።
የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዓለምአቀፍ ሕግን በሚጻረር መልኩ ከየመን ተላልፈው መሰጠታቸውና እስካሁን ድረስም በሕግ አለመዳኘታቸው የገዥው ፓርቲን አፈና በገሃድ ያሳያል ብሏል። የአቶ አንዳርጋቸውን ከተያዙ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ተጠናክሮ መቀጠሉን ሪፕሪቭ በሪፖርቱ አመላክቷል። አቶ አንዳርጋቸው አሁን ያሉበት ቃልቲ እስር ቤት ከመግባታቸው አስቀድሞ ማንነቱ በማይታወቅ እስር ቤት ውስጥ ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸውም አትቷል። አቶ አንዳርጋቸው እራሳቸውን እንዲከላከሉ ምንም ዓይነት የሕግ ከለላ ያልተሰጣቸው ሲሆን የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳዳሪዎች ቃሊቲ እንደማይገኙም ተናግረዋል።
ለእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አቶ አንዳርጋቸው ከታገቱበት ተለቀው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሪፕሪቭ ጠይቋል። ጉዳያቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የዳኝነት አካል እንዲታይም ሲል ሪፕሪቭ ጠይቅዋል። 100% የፓርላማ ወንበሮችን የተቆጣጠረው ገዥው ህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጥሞታል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መፈክር በማንገብ ድምጻቸውን በዓደባባይ አሰምተዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለው ሕዝባዊ እንቢተኝነትን በኃይል ለመፍታት የኢትዮጵያ ገዥዎች የሚወስዱት መጠነሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሪፕሪቭን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስዳቸው ዘግናኝ ግድያዎችን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጎቾች አውግዘውታል።
የሪፕሪቭ ዳሬክተር የሆኑት ማያ ፎአ እንዳሉት ”የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ዜጎችን ተኩሶ መግደሉ የሚያሳየው ነገር ቢኖር በፖለቲካ ተቃዋሚው በአንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል በቀላሉ ያመላክታል። በሕዝባዊ ማእበሉ ምክንያት ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት የእንግሊዝ መንግስትበአፋጣኝ ወደ እንግሊዝ እንዲመለሱ ማድረግ አለበት። አቶ አንዳርጋቸው የሞት ፍርድ ብያኔ ከመወሰኑ በፊት ጉዳያቸው እልባት ሊበጅለት ይገባል። አዲሱ የተማሪዎችና የዴሞክራሲ ለውጥ አቀንቃኞች ተቃውሞ የሚያመልክተው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ መንግስት በሕዝብ ተቀባይነት የሌለውና ለሕግ ልእልና የማይገዛ መውደቂያው እየተቃረበ መምጣቱን ሲሉ ዳሪክተሯ ስጋታቸውን ገልጸዋል!’