ነሃሴ ፬ ( አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተመድ ሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን እንደገለጹት በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የተፈጸሙት ሃይል የተሞላባቸው እርምጃዎች እንዲመረመሩ ጽ/ቤታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመነጋጋር ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የታሰሩት ዜጎች እንዲፈቱም ባለስልጣኑ ጠይቀዋል። በተመሳሳይ ዜናም ሜሪካና አውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግድያ እንዲያጣሩ ዋሽንግተን ፖስት ጠይቋል።
ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ርእሰ አንቀጽ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ሰብአዊ መብት ጥሰት ከልክ በማለፉ የአቦማ አስተዳደርም ሆነ የአውሮፓ ህብረት ጉዳዩን በገልለተኛ ወገን አጣርተው እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብሎአል።
የገዢው ፓርቲ ድርጊት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንደሌለው አሜሪካ ግልጽ ማድረግ ይገባታል ያለው ጋዜጣው፣ የአውሮፓ ህብረትም ለዲሞክራሲ መቆሙ በገሃድ የሚፈተንበት ወቅት ላይ ላይ መድረሱን ገልጿል።