ኢሳት (ነሃሴ 4, 2008)
በሳምንቱ መገባደጃ በኢትዮጵያ የተፈጸመው የ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ግድያ ምዕራባውያን ሃገራት ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ድጋፍ ዳግም እንዲያጤኑት የሚያደርግ መሆኑ አለበት ሲል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አቋሙን በሚያንጸግባርቅበት ርዕሰ-አንቀጽ ገለጸ።
በሃገሪቱ እየተካሄዱ ባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ አቋሙን ይፋ ያደረገው ይኸው አለም አቀፍ ጋዜጣ የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በሃገሪቱ እየተፈጸመ ያለው ግድያ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በይፋ ማወጅ እንዳለባቸው አሳስቧል።
በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ አስመልክቶ የአሜሪካ መንግስት ከቀናት በፊት ያወጣውን መግለጫ የተቸው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ፣ አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት የሃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ አለመጠየቁን አክሎ ኮንኗል።
ገዥው የኢትዮጵይ መንግስት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየገደለ ምዕራባውያን ሃገራት አሁንም ድረስ ድጋፋቸውን ለምን ይሰጣሉ ሲል የጠየቀው ጋዜጣው ከአሜሪካ በተጨማሪ ምዕራባውያን በሃገሪቱ ላይ ያላቸውን አቋም መፈተሽ እንዳለባቸው አስታውቋል።
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ከኢትዮጵያ የሚደረጉ ስደቶችን ለመቆጣጠር በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገንዘብ ለመለገስ ስምምነትን መፈጸሙን ያወሳው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ህብረቱ ግድያው እስካልቆመና ገለልተኛ ማጣራት እስከሚደረግ ድረስ ስምምነቱን ተግባራዊ ላለማድረግ ግልጽ አቋም መውሰድ አለበት ሲል በርዕሰ አንቀጹ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ ሃገሪቱ የሰብዓዊ መብትን ለማሻሻል ዕርምጃዎች እየተወሰዱና ለውጦች እንዳሉ ቢገልጹም፣ ምላሹ በገሃድ ከሚታየው ግድያ ጋር የማይገናኝ መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ልማትን አስመዝግባለች ተብላ እንደምሳሌ ስትጠቀስ ብትቆይም በተደጋጋሚ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በሚገልፁ ሰዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የሃይል ዕርምጃ ልማቱን አደጋ ውስጥ ከቶት እንደሚገኝ አለም አቀፉ ጋዜጣው በርዕሰ አንቀጹ አስነብቧል።
ይኸው አለም አቀፍ ጋዜጣ ባለፈው አመት በተመሳሳይ መልኩ የአሜሪካ መንግስትና ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለትን የፖለቲካ አካሄድ በመተቸት አቋማቸውን እንዲፈትሹ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ለወራት የዘለቀን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውና በ10 ሺ የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰው ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ለንባብ ባበቃው የአቋም መግለጫው አመልክቷል።