በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የጅምላ አፈሳ እየተካሄደ ነው ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 3 ፥ 2008)

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ የለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በአካባቢው የጅምላ አፈሳ በመካሄድ ላይ መሆኑን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

የክልሉ ፖሊስና የደህንነት ሃይሎች ጨለማን ተገን በማድረግ ተቃውሞን አስተባብረዋል ብለው የጠረጠሯቸውን አካላት በማሰር ላይ እንደሆኑ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር በደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች በአካባቢው ሰፍረው የሚገኙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡና ለሚጠሩ ስብሰባዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት የጸጥታ ሃይሎች እርምጃን በመውሰድ ላይ እንደሆኑ ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ የተለያዩ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አመራሮች ከነዋሪዎች ጋር ውይይትን ለማካሄድ ቢሞክሩም በነዋሪዎች ተቃውሞ ምክንያት ውይይቱ መጨናገፉን እማኞች አስረድተዋል።

በአመራሮቹና ነዋሪዎቹ መካከል ሊካሄድ የታሰበው ውይይት መጨናገፉን ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች መጠነ ሰፊ የጅምላ እስራት በማካሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በአካባቢው የሚገኙ የክልሉ ፖሊስ አባላትና ሚሊሺያዎች ነዋሪው በተለይ ወጣቱ ራሱን በማደራጀት እንዲንቀሳቀስ ጥሪ ማስተላለፋቸውን እማኞች አክለው አስታውቀዋል።

የሃይማኖች አባቶችን ጨምሮ የዞንና የወረዳ ባለስልጣናት በጎንደር እና ባህርዳር ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች የዕለት ከእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀጥሉ ሰኞ ጥረት መጀመራቸው ይታወሳል።

ይሁንና በሁለቱ ከተሞችና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች እየቀረበላቸው ያለን ጥሪ ባለመቀበል ስራ አለመጀመራቸውን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተቃውሞን እያካሄዱ ያሉ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱና ግድያና እስራት እንዲቆም እንዲሁም የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥያቄን እያቀረቡ ይገኛል።