በሳምንቱ መገባደጃ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በትንሹ 97 ሰዎች በላይ መገደላቸው ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 2 ፥ 2008)

በሳምንቱ መገባደጃ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተካሄዱ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ከ50 የሚበልጡ ሰዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የተኩስ ዕርምጃ ተገደሉ።

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የጸጥታ ሃይሎች በትንሹ 33 ሰዎች መግደላቸውና ተጨማሪ በርካታ ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሮይተርስ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘግቧል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ክልል ጎንደር እና ባህርዳር ከተማ እና ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት ተመሳሳይ ዕርምጃ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በሁለቱ ክልሎች ለሶስት ቀናት በተወሰዱ የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ በትንሹ ከ97 የሚበጡ ነዋሪዎች መገደላቸውንና በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ጸሃፊ የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ እስከ እሁድ ድረስ በተሰበሰቡ መረጃዎች ፓርቲው በትንሹ የ33 ሟች ሰዎችን ሊያረግጥ እንደቻለ ለሮይተርስ በሰጡት ቃለ-ምልልስ አውስተዋል።

ግድያው በትንሹ በ10 በሚሆኑ የክልል ከተሞች መፈጸሙን የተናገሩት ሃላፊው ሶስት የፓርቲው አባላትም ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ ከተሞች በፈጸሙት የሃይል እርምጃ ቁጥራቸው በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎችም ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ በአማራ ክልል ጎንደርና ባህርዳር ከተሞች እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በተፈጸመ ተመሳሳይ ድርጊት ከ20 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

የመንግስት ልዩ ሃይሎች በፈጸሙት በዚሁ ድርጊት በፅኑ የቆሰሉ በርካታ ሰዎች በህክምና ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አካላት ለኢሳት አስታውቀዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት አርብ በተደጋጋሚ ሊካሄዱ የታቀዱ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን ህገወጥ ናቸው ሲሉ ቢገልጹም ህዝቡ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱ ይታወሳል።

አዲስ አበባ ከተማ ቅዳሜ መስቀል አደባባይ ለተቃውሞ ከወጡ በርካታ ሰዎች መካከል በነዋሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙንና ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎችም ለእስር መዳረጋቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።