አቶ ደመቀ መኮንን በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱ ህዝባዊ ተቃውሞ ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ የተደረጉ የአመጽ ድርጊቶች ናቸው አሉ

ኢሳት (ነሃሴ 2 ፥ 2008)

በሳምንቱ መገባደጃ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱ ህዝባዊ ተቃውሞ ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ የተደረጉ የአመጽ ድርጊቶች ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ሰኞ ለመንግስት መገኛና ብዙሃን አስታወቁ።

የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ደመቀ በሁለቱ ክልሎች ለሶስት ቀናት ሲካሄዱ የነበሩ የተቃውሞ ሰልፎች “ህገወጥ” ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ሲካሄዱ የቆዩት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ በሃይል እና በጉልበት ስልጣን ለመቆጣጠር የተደረገ እንቅስቃሴ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ወ/ሮ አስቴር ማሞ በበኩላቸው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመመሳጠር የተቀነባበረ ነው ሲሉ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ቀናት ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ይህንኑ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ቢቢሲን ጨሞሮ አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያና ሮይተርስ፣ ኤቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲሁም በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘግብ ላይ ናቸው።