ህወሃት መራሹ መንግስት ህዝባዊ አመጹን በሃይል ለመቆጣጠር ባደረገው ሙከራ በአንድ ሳምንት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች  በግፍ ተገደሉ

ነሃሴ  ፪ ( ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሃት አገዛዝ በቃን የሚሉ ተቃውሞዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ተከትሎ ገዢው ፓርቲ ህዝባዊ አመጹን በመሳሪያ ለመጨፍለቅ እና የስልጣን እድሜውን ለማራዘም እጅግ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው። በዚህ የሃይል እርምጃ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች ከ150 በላይ ሰዎች መገደላቸው በብዙ መቶወች የሚቆጠሩ ዜጎች መቁሰላቸው ታውቋል።

በኦሮምያ በበርካታ ከተሞች ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ የአገዛዙ ወታደሮች ተኩስ ከፍተው ከ100 በላይ ሰዎችን ሲገድሉ፣ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም ሰኞ በደብረታቦር በባህርዳር እና በሌሎችም የሰሜን ጎንደር ከተሞች በተካሄዱ ተቃውሞዎች በድምሩ ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በጎንደር ከተማ ከደረሰው ከባድ እልቂት በመቀጠል ከፍተኛ እልቂት በደረሰበት በባህርዳር ከተማ የከተማው ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመውጣት ለውጥ እንፈልጋለን፣ አገዛዙ በቃን፣ የታሰሩት ይፈቱ፣ በቀለ ገርባ መሪያችን ነው፣ አንዳርጋቸው ጽጌ መሪያችን ነው፣ ብርሃኑ ነጋ መሪያችን ነው፤ ኮ/ል ደመቀ መሪያችን ነው፣ አንድ ነን አንከፋፈልም የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰማ ውሎአል። ከጊዮርጊስ አደባባይ እና አባይ ማዶ ከሚባሉት ቦታዎች ሆኖ ተቃውሞውን በከፍተኛ ጨኹት ሲያሰማ የዋለው የከተማው ህዝብ ከጎንደር እየገሰገሰ የመጣው ህዝብ ሊቀላቀለው አባይ ማዶ አካባቢ ሲደርስ ወታደሮች ተኩስ በመክፈታቸው ከፍተኛ እልቂት ደርሷል። የመንግስት መኪኖች ተቃጥለዋል። የስርዓቱ አንዳንድ ድርጅቶችም ወድመዋል። ህዝቡ ዛሬም ተቃውሞውን በመቀጠል ጎማ በማቃጠል መንገድ በመዝጋት ተቃውሞውን ሲያሰማ ውሎአል። የባህርዳር ወጣት ትግሉ እንደማይቆም የሌሎች አካባቢ ወጣቶችም እንዲነሱ እና ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ እያቀረበ ነው።

ጎንደር እና አካባቢውም እንዲሁ በከፍተኛ ወታደራዊ ቁጥጥር ስር የወደቀ ሲሆን፣ ወጣቱ እንደልብ መውጣትና መንቀሳቀስ አልቻለም። ዛሬም ተቃውሞ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ወታደሮች ወደ አካባቢው በመሄድ ተቆጣጥረውታል። ይሁን እንጅ ውጥረቱ አሁንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሰሜን ጎንደር ሰሮቃ ፣ አርማጭሆ፣ ሳንጃ በሚባሉት አካባቢዎች ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያለ ሲሆን፣ ትናንት በሙሴ ባምብ አካባቢ ህዝቡ ባደረሰው የደፈጣ ጥቃት 8 ወታደሮች ተገድለዋል። የጦር መሳሪያዎችም ተማርከዋል። እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ለመፈለግ ወታደሮች በአካባቢው ተሰማርተው አሰሳ እያደረጉ ነው። በትክል ድንጋይ አካባቢ ደግሞ ታጣቂዎች አድፍጠው በመጠበቅ በአንድ ኦራል በተጨኑ ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው 7 ወታደሮች ተገድለዋል። በርካታ የሞቱ ወታደሮች ወደ ጎንደር መወሰዳቸውን ምንጮች ግልጸዋል።

ትናንት በሰሮቃ የህወሃት ታጣቂዎች ወታደራዊ ልብስ ለብሰው ወደ ከተማ መግባታቸውን ተከትሎ ከሳንጃ፣ አርማጭሆ፣ እንዲሁም ከአብራሀጅራ፣ አብድራፊ እና ጎደቤ አካባቢ የተነሱ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ታጣቂዎች ሰሮቃ ደርሰው በአንድ ጄኔራል የተመራውን ጦር ከበው አርፍደዋል። ታጣቂዎቹ ህወሃት ይህን ከተማ ሊያስተዳድር አይገባውም ውጡልን ቢሉም ጄኔራሉ እናንተ እኔን አታስወጡኝም በማለቱ ፍጥጫው እያየለ ሲመጣ፣ የአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ በመግባት ታጣቂዎቹ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ያደረጉ ሲሆን፣ ዛሬ ግን እነዚህ ታጣቂዎች እኛ ከእንግዲህ በአባይ ወልዱ አንገዛም በማለት ከተማዋን ለቀው ጫካ ገብተዋል። ፍጥጫው እያየለ መምጣቱን ተከትሎ ሴቶችና ህጻናት ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርጓል። የአገዛዙ ወታደሮች እስካሁን ድረስ ደፍረው ተኩስ ለመክፈት አልቻሉም።

ከ3 እስከ 6 የሚደርሱ ታንኮችና የተለያዩ ከባድ መሳሪያዎችን ያነገቡ ወታደሮች በአካባቢው እየተንቀሰቀሱ ነው።

በኦሮምያም እንዲሁ  ሕዝባዊ እንቢተኙነቱ  በምእራብ ሸዋ ሙገርና ጉደር፣ በሆለታ፣በጉጂ፣ በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይ፣ በባሌና በአርሲ ዞኖች ቀጥሎ ውሎአል። በአወዳይ በታጣቂዎች በግፍ በተገደሉ ዜጎች የቀብር ስነስርዓት የተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን በከፍተኛ ቁጣ ሲያሰሙ ውለዋል።በሃሮማያ ዩንቨርሲቲ የክረምት ተማሪዎች  በግቢያቸው ግድያውና አፈናውን በመቃወምና በማውገዝ ሰልማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

በአርሲና በባሌ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን አረመኔያዊ ግድያ በማውገዝ ሰላማዊ ተቃውሞውና ሕዝባዊ እንቢተኝነቱን በመደገፍ ከሕዝባቸው ጋር መቆማቸውን ተናግረዋል።

በመላ አገሪቱ እየተካሄ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ብሄሮችን እርስ በርስ ለማጋጨት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። በባህርዳር እና በኦሮምያ ክልሎች አንዱ ለሌላው ያለውን ደግፍ ሲገልጽ ታይቷል።