ኢሳት (ነሃሴ 2 ፥ 2008)
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እየተከሰተ ያለውን ህዝባዊ ንቅናቄና መንግስት እየወሰደ ያለውን የግድያ እርምጃ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሽፋን ሰጡ። ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል፣ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ፣ ዶቼ ቬለ እና፣ ኤንዲ24 በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ከዘገቡት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይጠቀሳሉ።
ቢቢሲ ባሳለፈነው ቅዳሜና እሁድ በጎንደርና በባህርዳር ከተሞች ብዛት ያላቸው ዜጎች በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች መገደላቸውን ዘርዝሮ በድረ-ገጹ አስነብቧል። በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ጨሞሮ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል ያለው ቢቢሲ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ሰልፎቹ መሪ የሌላቸውና ህገወጥ ናቸው በማለት ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ህዝቡ የመንግስትን ማስፈራሪያ ሳይቀበለው በነቂስ ወደ አደባባይ መውጣቱን ዘግቧል።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት ኢህአዴግ መንግስት የሁለቱ ታላላቅ ብሄሮች ማለትም የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች በሰብዓዊ መብት ረገጣና በሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያደርጉ እንደነበር በዘገባው አስፍሯል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላማዊ ሰልፈኛ ባህርዳርን እንዳናወጣት የገለጸው የቢቢሲ ዘገባ፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። በእሁዱ ሰልፍ የመንግስት ሃይሎች አስለቃሽ ጋዝና ጥይት በሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ እንደተጠቀሙ ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።
ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በአዲስ አበባ ቅዳሜ የተደረገውን ሰልፍ አስመልክቶ ሰፊ ዘገባ አቅርቧል። ከ8 ወራት በፊት በኦሮሚያ የተጀመረው ይህ ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ በአማራ ክልልም ተጠናክሮ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል ሲል ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል በድረገጽ ዘገባው አስነብቧል። በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ስድስት ሰዎች በመንግስት ሃይሎች እንደተገደሉ የገለጸው ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል፣ ህወሃት በሚመራው መንግስት በሚደርስባቸው አድሎና መገለል በመማረር ለህዝባዊ እምቢተኝነት እንደተነሳሱ በዘገባው አስፍሯል።
ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን የሚቆጣጠሩትና የስራ ዕድል የሚያገኙት የህወሃት አባላት መሆናቸውን ሰላማዊ ሰልፈኞችን ዋቢ በማድረግ የገለጸው የዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል የዜና አውታር፣ የጸጥታና ደህንነት፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ ቦታዎችም እንዲሁ በትግራይ ሰዎች እንደተያዘ አክሎ ገልጿል።
ኤንዲ24 (ND24) የተባለውና በጀርመንኛ ቋንቋ የሚታተመው ጋዜጣ በሰራው ቪዲዮ እንደገለጸው፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል ግጭት ተከስቶ ብዛት ያለው ሰው መቁሰሉን አስፍሯል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር፣ የገበሬዎች መሬት እንዳይወሰድና፣ መሬት ወደ ሌሎች ክልል መወሰዱን ተቃውመዋል ሲል በዜናው አስፍሯል።
አልጀዚራ በበኩሉ ቅዳሜ በጎንደር የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ዘግቧል። ሁለት ሰው መገደሉን የገለጸው አልጀዚራ፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በኦሮሚያ ክልል ባሳለፍነት ቅዳሜ የተደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞ የገለጸው የአልጀዚራ ዘገባ፣ ብዛት ያላቸው ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች እንደተገደሉና ሌሎች ደግሞ እንደታሰሩ አማኞችን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አካትቷል።
በአዲስ አበባ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ “ነጻነት እንፈልጋለን፣ የፖለቲካ እስረኞችን ይለቀቁ” በማለት መፈክር ሲያሰሙ እንደነበሩና፣ በመጨረሻም በፖሊስ ሃይል መበተናቸው አልጀዚራ አትቷል።