በታንዛኒያ የሚገኙ 500 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ አለም አቀፍ ድጋፍ ተጠየቀ

ኢሳት (ሃምሌ 28 ፥ 2008)

የታንዛኒያ መንግስት በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ 500 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ አለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍን ጠየቀ።

የሃገሪቱ የስደተኛና ኢሚግሬሽን መምሪያ በየጊዜው ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ በመጨመር ላይ መሆኑ እንደገለጸ ዘሲትዝን የተሰኘ የታንዛኒያ ጋዚኤጣ ሃሙስ ዘግቧል። Ethiopians in Tanzania

በተለያዩ ጊዜያት ወደ ታንዛኒያ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያውያን በመንግስት የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣት ቢያጠናቅቁም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ሳይችሉ መቀረታቸው ታውቋል።

በስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ የተባሉትን 500 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የታንዛኒያ መንግስት የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ በይፋ መጠየቁ ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።

በሃገሪቱ የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ቃሲም ሱፊ በየጊዜው በኬንያ እና ታንዛኒያ በኩል ወደ አፍሪካ ለመግባት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት ታንዛኒያ ላቀረበችው ጥያቄ ምላሽን የሚሰጥ ከሆነ ድርጅቱ ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሃገራቸው ለመመለለስ እንቅስቃሴን እንደሚያደርግ ሃላፊው ዘ-ሲቲዝን ጋዜጣ ገልጿል።

ከሃገሪቱ በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጎረቤት ማላዊ፣ ዛምቢያና የተለያዩ ደቡባዊ የአፍሪካ ሃገራት በእስር ቤት ኣንደሚገኙ ታውቋል።

በማላዊ የሚገኙ ከ100 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት ስቃይ እየደረሰባቸው ነው በማለት የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባለፈው ወር ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው እንዲወሰዱ ዝመቻ መክፈታቸው የታወሳል።

በሶስት ወር እስር ቤቶች የሚገኙ እነዚሁ ኢትዮጵያውያን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የደረቅ ዳቦ አቅርቦት የሚደረግላቸው ሲ9ን፣ ኢትዮጵያውያኑ በከፋ የአካልና የጤና ችግር ውስጥ መሆናቸውን የማላዊ መገናኛ ብዙሃን በመዘግብ ላይ ናቸው።

ባለፈው ወር በስደት ላይ የነበሩ 19 ኢትዮጵያውያን በኮንጎ ድንበር ላይ በእቃ መጫኛ ተሽከርካሪ ውስት በመጓጓዝ ላይ እንዳሉ በመታፈን ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።