በእስራዔል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግስት በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም ሰልፍ ወጡ

ኢሳት (ሃምሌ 28 ፥ 2008)

ነዋሪነታቸው በእስራዔል እየሩሳሌም ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን  መንግስት በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም ሃሙስ በከተማዋ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።

ለአመታት የቆየው የማንነት ጥያቄ አፈና ሲካሄድበት መቆየቱን የተናገሩት ሰልፈኞች ወልቃይትና አማራ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ሲገልጹ አርፍደዋል። Israel

የተለያዩ መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበሩት ሰልፈኞች በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማውገዝ እየተካሄደ ላለው ህዝባዊ ንቅናቄ አጋርነታቸውን እንዳሳዩ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን ያካሄዱት ኢትዮጵያውያን በገዢው የኢህአዴግ መንግስት በበላይነት ተይዟል ወዳሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በማምራት የኮከብ ምልክት ያለበትን ሰንደቅ አላማ በማውረድ በመደበኛው ባንዲራ ሲቀይሩ ታይተዋል።

ነዋሪነታቸው በእስራዔል እየሩሳሌም ከተማ የሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል በማለት በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ተቃውሞን ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።

ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተካሄደውን ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህዝቡ ላነሳው ህጋዊ ጥያቄ ሰላማዊ ምላሽን እንዲሰጠው በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ባለፈው እሁድ በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ የጎንደርና የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት በወቃይት ጠገዴ የኮሚቴ አባላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንዲያቆም ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች ጥያቄያቸውን እያስተጋቡ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እየተነሳ ያለው የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ህዝባዊ መሰረት የሌለው ነው ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።

ይሁንና የወልቃይት ጠገዴ የኮሚቴ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽ በመቃወም ህዝቡ ያነሳው ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የተጀመረው ሰላማዊ ትግል ቀጣይ መሆኑን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።