ኢሳት (ሃምሌ 26 ፥ 2008)
ባለፈው እሁድ ዋሽንግተን ዲሲ ሲደርሱ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበባቸው የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚደንትን በተመለከተ የትግራይ ተወላጆች በሰሜን አሜሪካ ማህበር መግለጫ አወጣ። ማህበሩ ባወጣው በዚህ መግለጫ ሻዕቢያና ትምክህተኞችን በመተባበሩ የፈጸሙት ተግባር ነው ሲሉ በትግራይ ክልል ም/ፕሬዚደንት ላይ የደረሰውን ተቃውሞ አውግዟል።
ረቡዕ ሃምሌ 27, 2008 በሚጀምረው የትግራይ ተወላጆች በሰሜን አሜሪካ በዓል ላይ ለመገኘት እሁድ ሃምሌ 24, 2008 ዋሽንግተን ሲደርሱ ተቃውሞ የቀረበባቸው የትግራይ ክልል ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ በህወሃት ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ ቀውስ ተከትሎ የትግራይ ተወላጆችን ለማረጋጋትና ድጋፍ ለማሰባሰብ መምጣታቸው ታውቋል።
ከረቡዕ ሃምሌ 27, 2008 እስከ እሁድ ነሃሴ 1 ፥ 2008 በሚቆየው የትግራይ ተውላጆች የሰሜን አሜሪካ ፌስቲቫል ላይ የሚገኙት ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ወደ ዋሽንግተን የሚገቡ የህወሃት ደጋፊዎች ተጠቃለው መግባታቸውን ተከትሎ የትግራይ ክልል ም/ፕሬዚደንት በህወሃት እንዲሁም በአጠቃላይ በትግራይና በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ቅዳሜ ከሰዓት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ማብራሪያ እንደሚሰጡ መረዳት ተችሏል።
በፌስቲቫሉ ላይ ለማይገኙ የትግራይ ተወላጆችን ለማገኝነት ደግሞ በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅተዋል። በህወሃት ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ ከሚደበቅበት ደረጃ እያለፈ መገኘቱ የህወሃት የጦር አዛዦች በነጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ እየተገለጸ መምጣቱን ተከትሎ በህወሃት ደጋፊዎች ስጋት መፈጠሩ እየተሰማ ይገኛል።
በውጭ ሃገር በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በሆኑ የህወሃት ደጋፊዎች ዘንድ የተፈጠረው ስጋት ለመቅረፍና ደጋፊ ለማሰባሰብ መምጣታቸው የተገለጸው የትግራይ ክልል ም/ፕሬዚደንት አዲስ አለም ባሌማ፣ በአጠቃላይ 23 ቀናት ያህል ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። በቆይታቸው በሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ ከውሃ ሃብት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ መርሃ ግብር ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል።
ለ23 ቀናት ቆይታ ዕሁድ ሃምሌ 24 ፥ 2008 ዋሽንግተን ዳለስ አለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርሱ በደረሰባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደናገጡ የታዩት ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ ተቃውሞውን መቋቋም ባለመቻላቸው ወደመጡበት ተመልሰው ሲገቡ የታዩ ሲሆን፣ በፖሊስ ድጋፍ ከገቡበት ወጥተው ለመሄድ ችለዋል።
የትግራይ ተወላጆች በሰሜን አሜሪካ ማህበር በድርጊቱ ተቆጥቶ ሰኞ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ድርጊቱ ሻዕቢያና ትምክህተኞች በትብብር የፈጸሙት ነው ሲልም ወቅሷል።