በሱዳንና ግብፅ ድንበር 600 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢሳት (ሃምሌ 26 ፥ 2008)

የሱዳን መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሃገሪቱ ከሊቢያ እና ከግብፅ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ 600 ኢትዮጵያውያን ስደተኖችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ሰኞ አስታወቁ።

ሃገሪቱ በሰኔ ወር ህገወጥ የተባሉ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ልዩ የጸጥታ ሃይሏን በድንበር አካባቢ ያሰፈረች ሲሆን፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በዚሁ ዘመቻ እየተያዙ መሆኑን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ወታደራዊ ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።Sudan Ethiopia border

የሱዳን የድንበር ልዩ የጸጥታ ሃይሎች ተወካይ የሆኑት ኮማንደር ሞሃመድ ሃምዳን-ዳግሎ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 600 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨማሪ ህገወጥ የስደተኛ አዘዋዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ለሰሜን ዳርፉር ግዛት ተላልፈው መሰጠታቸውን የገለጹት ሃላፊው፣ ኢትዮጵያውያኑ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል።

የሱዳን መንግስት እያካሄደ ባለው በዚሁ ዘመቻ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ሪፖርትን ያወጣው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሱዳን ከመቼውም ጊዜ በላይ የስደተኞች መዘዋወሪያ እየሆነች መምጣቱን በመግለጽ ሃገሪቱ እርምጃን እንድትወስድ አሳስቧል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እና በርካታ የስደተኛ ተቋማት ከኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ስደተኞች በጎረቤት ሱዳን በኩል ወደ ተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ወደ አውሮፓ በሚገቡ ህገወጥ ስደተኞች ስጋቱን በመግለጽ ላይ የሚገኘው የአውሮፓ ህብረት፣ ሱዳን ህገወጥ ስደተኞችን ለመግታት ለምታደርገው ጥረት በተያዘው አመት የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ይታወሳል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በበኩላቸው የፖለቲካ ጥገኝነትን ፈልገው ከሃገራቸው በመሰደ ላይ ያሉ ሰዎች ያለፍላጎታቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ አሳስቧቸው እንደሚገኝ በመግለጽ ላይ ናቸው።