አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ ሁለት ሃላፊዎች በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ተባሉ

ኢሳት (ሃምሌ 26 ፥ 2008)

ከሶስት አመት በፊት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ ሁለት ሃላፊዎች በተመሰረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ተባሉ።Melaku Fenta

ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሚኒስትር ደረጃ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ እንዲሁም አቶ ገብረዋህድ ወደጊዮርጊስና አቶ በላቸው በየነ የቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ሲል ማክሰኞ ብይን ሰጥቷል።

ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ፈንታ ከሌሎች የስራ ባልደርቦቻቸውንና ባለሃብቶች ጋር በመተባበር በታክስ ማጭበርበር ጋር በተገናኘ መንግስት ማግኘት የነበረበትን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል ተብለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወቃል።

ሚኒስትሩ የቀረበባቸውን ክስ እንዲያስፈጽሙ በመቃወም ክርክርን ሲያካሄዱ የቆዩ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ የቀረቡ ማስረጃዎች ክሱን የሚያረጋግጡ ናቸው በማለት ተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ማስተላለፉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በአማራ ባለስልጣናት በሃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ መርክነት አለማየሁ፣ አቶ እሸቱ ግርፍ፣ አቶ አስፋው ስዩም፣ እና አቶ አስመላሽ ወልደማሪያም ተመሳሳይ ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ባለሃብቱ የኬኬ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ ከሃላፊዎቹ ጋር ክሳቸውን እንዲከላከሉ ተብለው ብይን ተላልፎባቸዋል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ ክስ ውስጥ የቆዩትን የኢንተርኮንቲኔንታል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደን የአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅን መሰረት በማድረግ ከተመሰረተባቸው ክስ በነጻ እንዳሰናበታቸው ታውቋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት መስከረም 30 ቀን 2009 አም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከ50 የሚበልጡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሃብቶች ከሶስት አመት በፊት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ነው።